ለአገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎችን ለመለየት የተባባሪ አካላት ሚና የጎላ ነው - አገራዊ የምክክር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
ለአገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎችን ለመለየት የተባባሪ አካላት ሚና የጎላ ነው - አገራዊ የምክክር ኮሚሽን
አዳማ ፤ ታህሳስ 4/2016(ኢዜአ)፡- ለአገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎችን ለመለየት የሚደረገውን ሂደት ለማሳካት የተባባሪ አካላት ሚና የጎላ መሆኑን የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ የተሳታፊዎች ልየታ ስራ የሚያከናውኑ የተባባሪ አካላት ስልጠና በአዳማ አባገዳ አዳራሽ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በስልጠናው ማስጀመሪያ መድረክ ላይ እንደገለጹት፤ አለመግባባቶችን ለመፍታት አገራዊ የህዝብ ምክክሮችን አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ ለማስኬድ እየተሰራ ነው።
ይህም ወቅታዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን መሆኑን አመልክተው፤ የፖለቲካና የማህበራዊ መደላድል ለማመቻቸትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ነው ብለዋል።
በዚህም አመርቂ ውጤት ላይ የሚደረሰው ከሲቪክ ማህበራትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ፍትሃዊና አካታች በሆነ መንገድ የምክክሩ ተሳታፊዎችን መለየት ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ይህንን ወሳኝ ተግባር በአግባቡ ለመፈፀም ከኮሚሽኑ ጋር ሆነው ተሳታፊዎችን የሚለዩ የተባባሪ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።
የአዳማው መድረክም በኦሮሚያ ክልል ተሳታፊዎችን ለመለየት ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር የሚሰሩ አካላትን በማሰልጠን ወደ ተግባር እንቅስቃሴ ለመግባት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ተባባሪ አካላቱም ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከመምህራን፣ ከዕድሮች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከአባገዳዎችና ሃዳ ሲንቄዎች እንዲሁም ከመንግሥት የአመራር አባላት የተለዩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በዛሬው መድረክ የተሳተፉት ከስምንት የክልሉ ዞኖችና ከሸገር ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ መሆናቸውንም አክለዋል።
በስልጠናው በአገራዊ ምክክር ምንነት፣ አካሄድና የሚጠበቁ ውጤቶች እንዲሁም ተሳታፊዎችን የመለየት ስነ ዘዴ ላይ በቂ ግንዛቤ አግኝተው የድርሻውን እንዲወጡ እንደሚያስችል ተስፋ መደረጉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ቀደም ሲል በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የተባባሪ አካላት ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል።