የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነው - ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ ነው - ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሁሉም ዘርፎች ከአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጽያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው።
በፎረሙ የአፍሪካ አገራት አየር ኃይል አዛዦች፣ የተለያዩ አገራት የአቪዬሽን ተቋማት ኃላፊዎችና ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል "በመስዋዕትነት አገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ኃሳብ ከሕዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።
የመርኃ ግብሩ አንድ አካል የሆነው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም በመካሄድ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ የረጅም ዓመት ታሪክ ያላትና ቅኝ ያልተገዛች አገር ናት ብለዋል።
አየር ኃይሉ በርካታ የአፍሪካ አገራትን በአየር ኃይል፣ በልምምድና በአየር ትራንስፖርት ዘርፎች እገዛ ሲያደርግ እንደነበር ጠቁመው ይህንንም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በቀጣይም የጀመራቸውን ሥራዎች ይበልጥ በማጠናከር በሁሉም ዘርፎች ከአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑ ጠቁመዋል።
ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባለፉት አምስት ዓመታት በሰው ኃይል፣ በትጥቅ ማዘመንና በሌሎች ዘርፎ በርካታ የለውጥ ሥራውችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በፎረሙ በአፍሪካ የአየር ኃይል ዕድገት ላይ ሊገጥም የሚችሉ ተግዳሮቶችን በጋራ መፍታት በሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ዙሪያ ምክክር ይደረጋል ተብሏል።