በመንግስት ከፍተኛ ወጪ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን ከብክነትና ከጉዳት መጠበቅ የሁላችንም ድርሻ መሆን አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በመንግስት ከፍተኛ ወጪ የተገነቡ መሰረተ ልማቶችን ከብክነትና ከጉዳት መጠበቅ የሁላችንም ድርሻ መሆን አለበት
ቦንጋ/ሀረር/ጅማ ፤ ታህሳስ 4/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወጪ ያወጣችባቸው መሰረተ ልማቶችን ከብክነትና ከብልሽት መጠበቅ የሁሉም ሃላፊነት መሆን እንዳለበት ነዋሪዎችና የዘርፉ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።
በአገሪቱ መንገድም ሆነ ሌሎች መሰረተ ልማቶች በተለያየ ምክንያት ማገልገል ከሚገባቸው ጊዜ በፊት ለብልሽት ተዳርገው አሊያም ተሰርቀው ለከፍተኛ ጉዳት ሲዳረጉ ይስተዋላል።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ ኢዜአ በጅማ፣ ቦንጋና ሀረር ከተሞች በመንገድ፣ በኤሌክትሪክና በቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ምን መደረግ እንዳለበት ነዋሪዎችንና የስራ ኃላፊዎችን ጠይቋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅማ ከተማ ነዋሪዎች በተለይም የኤሌክትሪክና የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች በተለያየ መልኩ በሚያጋጥማቸው ጉዳትና ብልሽት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር አየፈጠረ መሆኑን ይገልጻሉ።
አስተያየታቸውን የሰጡት የጅማ ከተማ ነዋሪዎቹ አቶ መሀመድ ከድር እና ወጣት ሱዲ አብዱል ቃድር በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በተለያየ መልኩ ጉዳት ሲደርስ መታዘባቸውን ተናግረዋል።
የመብራት ምሰሶና ሌሎች የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ተሰርቀው በህገወጥ መንገድ ለብክነት ሲዳረጉ መመልከታቸውንም እንዲሁ።
እንደ ነዋሪም ሆነ እንደ አገልግሎት ፈላጊ ችግሩን በተመለከተ ለተቋሙ መረጃ ቢሰጡም አፋጣኝ ምላሽ እንደማይሰጥና አጥፊዎችም ተጠያቂ ሲሆኑ አለመመልከታቸውን ተናግረዋል።
የተቋሙ ሰራተኞችም ይሁኑ ህብረተሰቡ የኤክትሪክ መሠረተ ልማቶችን በባለቤትነት ስሜት በመጠበቅ የሚደርሱ ጉዳቶችንና ስርቆቶችን መከላከል እንደሚገባም አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጅማ ዲስትሪክት ሀላፊ አቶ ሲሳይ ሰቦቃ፣ በጅማና አካባቢው በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል።
በዲስትሪክቱ 14 አገልግሎት መስጫ ማዕከላት እንዳሉ ጠቅሰው በእነዚህ ማዕከላት ለሚሰጡ አገልግሎቶች የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ቀላል አይደለም ብለዋል።
በተለይም በመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ምክንያት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጸው ስርቆትና ውድመት ደግሞ ሌላኛው የችግሩ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሰረተ ልማቶቹ ላይ ጉዳት ያደረሱትን አካላት ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው በዋናነት ችግሩን ለመቅረፍ ሁሉም ዜጋ እነዚህን መሰረተ ልማቶች በባለቤትነት መጠበቅ እንዳለበት ገልጸዋል።
በኤሌክትሪክ አገልግሎት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የስርጭት፣ ኦፕሬሽን እና ጥገና ሀላፊ አቶ እስራኤል ሀብታሙ፣ በአካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል።
ከእነዚህ መካከልም የኤሌክትሪክ መስመር ከዛፍ ጋር በመነካካት የሚፈጥረው ጉዳት እንዲሁም የመሰረተ ልማት ስርቆቶች ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
በ2015 ዓ.ም ብቻ በአካባቢው በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ወደ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት እና ስርቆት ማጋጠሙን ገልጸው ወንጀሉን የፈፀሙ አካላትን ለህግ አቅርቦ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ ሀብት ላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚፈፀሙ የስርቆትና ሌሎች ጉዳቶችን በጋራ መከላከል እንደሚገባም አመልክተዋል።
መሠል ድርጊቶች በኢትዮ ቴሌኮም መሠሰረተ ልማቶች ላይም የሚከሰቱ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በሀረሪ ክልል በኢትዮ ቴሌኮም የማዕከላዊ ምስራቅ ሪጅን ሪጅናል ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሰኢድ ናቸው።
ለተቋሙ አገልግሎት መስጫ የሚውሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እቃዎች በውጭ ምንዛሬ የሚገዙ መሆናቸው ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል ብለዋል።
መሠረተ ልማቶቹ በስርቆት፣ በግዴለሽነት እና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዘንድ ባለመናበብ ምክንያት ተገቢውን ጥቅም ሳይሰጡ የሚወድሙበትና የሚበላሹበት ሁኔታ መኖሩንም አረጋግጠዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እና በህብረተሰቡ ዘንድ በአገልግሎት ጥራት መጓደል ምክንያት የሚነሳው ቅሬታ ከፍተኛ እንደሆነም አብራርተዋል።
ይሄንን ድርጊት ለመከላከል ከፀጥታ አካላት እና ከአካባቢው አስተዳደሮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ቢሆንም ተጠያቂነትን ከማስፈንና የደረሰውን ጉዳት ካሳ ከማስከፈል አንፃር የተፈለገውን ያክል ውጤት እየመጣ አለመሆኑንም አስረድተዋል።
የኢዜአ ሪፖርተሮችም መንገድን ጨምሮ በተጠቀሱት መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ባደረጉት ምልከታ አረጋግጠዋል።
ያነጋገርናቸው የስራ ኃላፊዎችም እነዚህን መሰረተ ልማቶች ከጉዳትና ውድመት ለመታደግ ሀላፊነቱ የእያንዳንዱ ዜጋ መሆን እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።