የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 04/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በማስመልከት የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም 'Future African Airforce' በሚል መሪ ሀሳብ በቢሾፍቱ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል አዛዦች፣ የተለያዩ ሀገራት የአቪዬሽን ተቋማት ኃላፊዎችና ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።
" በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአየር ምድቦችና ሁነቶች ሲከበር መቆየቱ ይታወሳል።
የዚህ መርሐግብር አካል የሆነ የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች የምክክር መድረክ (ፎረም) 'Future African Airforce' በሚል መሪ ቃል በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የመድረኩ አላማም በኢትዮጵያ አየር ኃይል ከለውጡ ወዲህ የተሰሩትን ሥራዎች ማስተዋወቅና የዘርፉን ሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር መሆኑ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይልም ከአፍሪከ አየር ኃይል ተቋማት ጋር የትብብር ስምምነት ፊርማ እንደሚያካሂድም ተጠቁሟል።
ከመርሐግብሩ ጎን ለጎን አየር ኃይሉ ያስገነባቸው የውጊያ መሠረተ-ልማቶች እንዲሁም የትጥቅ አቅምን ለማሳደግ የተሰሩ ሥራዎች ጉብኝት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
በአየር ኃይሉ ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የትጥቅ አቅምን በማዘመን እና በመሠረተ-ልማት ግንባታ ረገድ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸው በመድረኩ ተገልጿል።
በመድረኩ የተለያዩ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የትብብር ግንኙነት የሚያሳዩ ጥናቶች እንዲሁም ልዩ ልዩ ሰኖዶች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።
በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሠረተበትን ኅዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም በመነሻነት ተወስዶ ዘንድሮ 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል እየተከበረ ሲሆን ታኅሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የበዓሉ የማጠቃለያ መርሐግብር ይካሄዳል።