ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይከናወናሉ 

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 4/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስምንተኛ ሳምንት  መርሐ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ሃዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

9 ነጥብ በመያዝ 8ኛ ደረጃን ላይ የሚገኘው ሃዋሳ ከተማ  በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።


 

ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል።

ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ ሲያሸንፍ በአንዱ ሽንፈት ገጥሞታል፤  አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያላቸው ፈረሰኞቹ በ13 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ሌላኛው የስምንተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ወልቂጤ ከተማና መቻል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይገናኛል።


 

ወልቂጤ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ተሸንፏል፤ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ክለቡ በ8 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በ16 ነጥብ በሊጉ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቻል ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

የስምንተኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ፋሲል ከነማ ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ 9 ሰዓት፤ ድሬዳዋ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ከምሽቱ 12 ላይ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊጉን በ17 ነጥብ እየመራ ይገኛል።

 የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ታህሳስ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም