ቀጥታ፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክር ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ታህሣስ 04/2016 (ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ረዳት ዋና ዳይሬክተር ቫለሪ ጓርኔሪ ጋር በጄኔቫ ውይይት አድርገዋል፡፡

ከ2ኛው ዓለም አቀፍ የሥደተኞች ፎረም ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት ሁለቱም ወገኖች የተሻሻለውን የዕርዳታ ስርጭት ሥርዓት በመጠቀም ድጋፉን የበለጠ ለማፋጠን ተስማምተዋል።

መንግሥት ድጋፉ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ብቻ እንዲደርስ ማድረግ የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱን አረጋግጠው የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የዕርዳታ አቅርቦትን በድጋሚ በመጀመሩም አመስግነዋል፡፡

ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታትም የዘላቂ ልማት መርሐ-ግብሮች አስፈላጊ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብርና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ እንደሚገኙም አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

ቫለሪ ጓርኔሪ በበኩላቸው ውጤታማ የዕርዳታ ስርጭት ሥርዓትን በማሻሻል ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት ላደረገው ትብብርና ቁርጠኝነት አመስግነዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራምም ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም