ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የአገር ውስጥ የኃብት ማሰባሰብ ሥራውን ሊያጠናክር ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የሰብዓዊ ድጋፉን ውጤታማ ለማድረግ የአገር ውስጥ የኃብት ማሰባሰብ ሥራውን ሊያጠናክር እንደሚገባ ተጠቆመ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምን ገምግሟል።


 

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በተለያዩ አደጋዎች ለሚደርሱ ጉዳቶች የሚደረገውን የሰብዓዊ ድጋፍ ውጤታማ ለማድረግ የአገር ውስጥ አቅም ለመፍጠር በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የመረዳዳት ባህሉ የበለጠ እንዲሻሻል የሚከናወኑ ተግባራት መጠናከር እንዳለበት ገልጸው፤ ተረጂዎች ምርትና ምርታማነት ላይ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ በማድረግ የተረጂነት አመለካከት ለመቅረፍ የተጀመሩ ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባልም ነው ያሉት።

ኮሚሽኑ የውስጥ አቅምን ከማደራጀት በተጨማሪ አጋርነት፣ ቅንጅትና ትብብርን የበለጠ በማጠናከር የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉም አሳስበዋል።

ቀልጣፋና ውጤታማ የአደጋ ምላሽ ሥርዓት በመዘርጋት የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት የተጀመረውን የተቋሙ ሪፎርም ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚገባም ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ልማትን በማካተት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚሆን በቂ የእህል ክምችት መኖሩን ጠቁመው፤ ነገር ግን የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ለማጓጓዝ ችግር መሆኑን ተናግረዋል።

በሩብ ዓመቱ ከዚህ በፊት በመንግሥትና በአጋር አካላት ሲደረግ የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ በመንግሥት አቅም ብቻ ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።

ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ሰብዓዊ እርዳታ የማቅረብ ሥራ የጎላ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ ተቋማትን ጨምሮ ሕብረተሰቡ በሂደቱ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ይሰራል ነው ያሉት።

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም