ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ አምርቶ በመተካት የተመዘገበው ውጤት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የሚሻ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ አምርቶ በመተካት የተመዘገበው ውጤት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የሚሻ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ)፡- ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ አምርቶ በመተካት የተመዘገበው ውጤት የተጠናከረና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የሚሻ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።
የእኛ ምርት አምራች ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር "ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ኃሳብ በዛሬው እለት ተከፍቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ ኢትዮጵያ ወደ ኃብት ሊቀየሩ የሚችሉ የበርካታ የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት ብትሆንም እስካሁንም በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በርካታ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የተፈጥሮ ፀጋን ወደ ኃብት ለመቀየር የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ገበያና ፈጠራ እንዲሁም አገራዊ ፍላጎትና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን አመዛዝኖ መሥራት የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአምራች ኢንተርፕራይዞች መንግስት በሰጠው ትኩረትም አሁን ላይ በርካታ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት ተችሏል ብለዋል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ አምርቶ በመተካት የተመዘገበው ውጤት በቀጣይነት የተጠናከረ ድጋፍ ያስፈልገዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊየን ዶላር በማውጣት ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ መተካት መቻሉን የገለጹት አፈጉባኤው ለተመዘገበው ስኬት የመንግሥትን ድጋፍና እገዛ አድንቀዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ድርሻና ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚችሉ የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ ምቹ የልማት ካበቢ ለመፍጠር ይሰራል ሲሉም አረጋግጠዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ መንግሥት በአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱ ከለያቸው አምስት የኢኮኖሚ የትኩረት መስኮች የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አንዱ ነው ብለዋል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ በማድረግ ተጭባጭ ለውጥ አስመዝግቧል፤ ቀጣይነትም ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ መጨረሻ ወደ ውጭ ከሚላክ ምርት ከ9 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል፤ ዘርፉ በገበያው ላይ ያለው 35 በመቶ ድርሻ ወደ 65 በመቶ የማሳደግ ግብ ተቀምጧልም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከ370 በላይ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ በማስገባት የአምራች ኢንተርፕራይዞችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ ጨምሮ ከውጭ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ከ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ ማዳን እንደተቻለ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ መንግሥትም በዘርፉ የነበሩ የአሰራር ማነቆዎችን አስተካክሏል ብለዋል።
ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ገቢ ምርትን የሚተካ፤ የቆዳ ኃብትን የሚያሻሽል፤ የአቅም ግንባታና የኮሙኒኬሽን ማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት የአሠራር ማሻሻያዎችን በማድረግ የብድር አቅርቦት፣ የመሠረተ-ልማት ግንባታና የገበያ ትስስር በመፍጠር ዘርፉን እየደገፈ ነው፤ ቀጣይነትም ይኖረዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የኢንተርፕራይዞችን ምርትና ምርታማነት ማሳደጉን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በለውጡ ዓመታት ኢንተርፕራይዞችን ቁጥር ከ26 ሺህ በላይ በማድረስ ከ570 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏልም ብለዋል።