በንግድ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በየሦስት ወሩ እየተገናኘ የሚነጋገር የመማክርት ጉባዔ ተመሠረተ - ኢዜአ አማርኛ
በንግድ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በየሦስት ወሩ እየተገናኘ የሚነጋገር የመማክርት ጉባዔ ተመሠረተ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ)፦ በንግድ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በየሦስት ወሩ እየተገናኘ የሚነጋገር ከግሉ ዘርፍና ከመንግሥት ተቋማት የተውጣጣ የመማክርት ጉባዔ ተመሠረተ።
የመማክርት ጉባዔው የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አመራሮች የተካተቱበት ሲሆን፤ ጠቅላላ ጉባዔና ሰባት አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ይኖረዋል ተብሏል።
ለዚህም የአገልግሎት አሰጣጥ የመማክርት ደንብ የፀደቀ ሲሆን፤ በየሦስት ወሩ በመገናኘት የንግዱን ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ የሚወያዩ ይሆናል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ የመማክርት ጉባዔው መመስረት ያስፈለገው ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀውን የንግድ አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመንና ለማሻሻል ነው ብለዋል።
በመሆኑም የግሉን ሴክተር ተወካዮች ያካተተው የመማክርት ጉባዔ የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ በየሦስት ወሩ እየተገናኘ በስፋት የሚወያይ መሆኑን ገልፀዋል።
በየመድረኮቹም በጠንካራ እና ደካማ ጎኖች የሚነሱትን ሃሳቦች በማሰባሰብ የንግዱን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ዘመናዊ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የመማክርት ጉባዔው ለተገልጋይ በተለይም የተገልጋዮች የቅሬታ ምንጭ የሆኑ ነገሮችን በመለየት ፈጣን ማሻሻያ እንዲደረግባቸው የሚያግዝ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ከማሻሻል ባለፈ የመንግሥትን ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በተገቢው መንገድ ተፈጻሚ ለማድረግ የላቀ ሚና እንደሚኖረውም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም የመማክርት ጉባዔ መመስረቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮችን የሚያቃልል ስለመሆኑ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ዘላለም ዘውዴ፤ የመማክርት ጉባዔው በአምራቾች፣ በሸማቾች እና በመንግሥት መካከል ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ እና የተቀናጀ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የአገልግሎት አሰጣጥ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰይድ መንዲሶ፤ የጉባዔው መመስረት በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም በቀጣይ የጉባዔው አባላት በንግዱ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ፈጣን እልባት እንዲኖር መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።