የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አራት አምቡላንሶችን ለወረዳዎች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አራት አምቡላንሶችን ለወረዳዎች ድጋፍ አደረገ
ዲላ፤ ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የጌዴኦ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በ8 ሚሊዮን ብር ወጭ የገዛቸውን 4 አምቡላንሶች በዞኑ ላሉ ወረዳዎች ድጋፍ አደረገ።
በርክክቡ ወቅት የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደሩ የኢኮኖሚ አማካሪና የክልሉ ቀይ መስቀል ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ማሄ ቦዳ " ማህበሩ ለነፍስ አድን ስራ ቅዲሚያ መስጠቱ ተገቢነት ያለውና የሚደነቅ ነው" ብለዋል።
ማህበሩ የሚሰጣቸውን አገልግሎት ለማስፋት የአባላት ተሳትፎን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ማህበሩ የሚያደርጋቸውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የክልሉ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።
በቀይ መስቀል ማህበር በኩል ለአገልግሎት የቀረቡት የአምቡላንስ ተሽከርካሪዎችም ለታለመለት ዓላማ ብቻ ሊውሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በማህበሩ የጌዴኦ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፈ አቶ ወንደሰን ዳካ በበኩላቸው ድጋፉ ማህበሩ በዞኑ በአንድ አምቡላንስ ብቻ ሲሰጥ የነበረውን የነፍስ አድን ስራ ወደ አምስት አምቡላንሶች ያሳድገዋል ብለዋል።
በማህበሩ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው አምቡላንሶቹም በጌዴኦ ዞን ለሚገኙ ይርጋጨፌ፣ ራጴ፣ ገደብና ኮቼሬ ወረዳዎች የተሰጠ ሲሆን ከተማ አስተዳደሮችም በጋራ እንደሚጠቀሙት ገልጸዋል፡፡
የአምቡላሶቹ ወደ ስራ መግባት በዞኑ በሰው ስራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች በሚከሰቱ ችግሮች የሚደርሰውን ጉዳት ለማዳን ያግዛል ብለዋል።
በተለይም ነብሰጡር እናቶችን ወደ ጤና ተቋም ለማድረስና መሰል የነፍስ አድን ስራዎችን ለማከናወን የሚደረገውን ጥረት እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።
የራጴ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታምራት ዴሌቦ ድጋፉ የተቀላጠፈ የነፍስ አድን ስራ ለማከናወን እገዛው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ምስጋናም አቅርበዋል።
በርክክቡ ወቅት አባ ገዳዎች፣ የዞን መምሪያ ኃላፊዎች፣ የወረዳና የከተማ አስተባባሪዎችና አፈ ጉባኤዎች ተገኝተዋል።