ቀጥታ፡

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሐረሪ ክልል ያካሄደው የተሳታፊዎች ልየታ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያካተተ ነው

ሐረር፤ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ)፡- አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሐረሪ ክልል ያካሄደው የተሳታፊዎች ልየታ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያሳተፈና አካታች መሆኑን የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች  ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀረሪ ክልል ያከናወናቸውን የተሳታፊዎች ልየታ እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራትን ተመልክቷል።


 

የቋሚ ኮሚቴው የምልከታ ቡድን አስተባባሪ ወይዘሮ አቡኔ አለም የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ አለመግባባቶችን ለመቅረፍና ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ለማጎልበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ የተቋቋመ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱም በኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጣ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የጉብኝቱም ዋና ዓላማ በክልሉ በዝግጅት ምዕራፎች የሁሉም ዜጋ ተሳትፎና የሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል አካታችነት የማረጋገጥ ስራ መመልከታቸውን አንስተዋል።

በምልከታውም ክልሉ የተለያዩ ብሔሮች የተሰባጠሩ ሕዝቦች የሚኖሩበት እንደመሆኑ ከብሔር ውክልና፣ ሁሉንም  ማህበረሰብ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የተሄደበት ርቀት አበረታች ነው ብለዋል።

እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል  በዴሞክራሲያዊ መንገድ ውይይት አካሄዶ ይወክለኛል ያለውን መምረጡን ተናግረዋል። 

ኮሚሽኑ እያከናወነ የሚገኘውን ስራ ማህበረሰቡ "ተረድቶታል ወይ" የሚለው ስራ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።


 

የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ተመስገን አምባቸው በበኩላቸው የተባባሪ አካላትና የተሳታፊዎች ልየታና ስልጠና አጠቃላይ አሳታፊነቱና አካታችነቱ ላይ ችግሮች እንዳልተመለከቱ ተናግረዋል።

በሂደቱ ላይም የክልሉ ህዝብን ሊወክሉ የሚችሉ መለየታቸውን ባገኟቸው መረጃዎች ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በክልሉ የተሳታፊዎች ልየታና ማህበረሰቡን ወክለው አጀንዳ የሚሰጡ ተሳታፊዎችን የማስመረጥ ስራ ማከናወኑን የተናገሩት ደግሞ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ አበራ ጀማዬ ናቸው።


 

የልየታ ስራውም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያሳተፈና ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ ከሚገኙ የሲቪል ማህበራት፣ አጀንዳ ከሚሰጡ እና የወረዳ ተባባሪ አካላትና ሌሎች ባለድርሻ ጋር እየተወያየ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም