"የመደመር ጉዞ'' የፓናል ውይይት ነገ በቦንጋ ከተማ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
"የመደመር ጉዞ'' የፓናል ውይይት ነገ በቦንጋ ከተማ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ) ፦ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከኢዜአ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው "የመደመር ጉዞ'' ፓናል ነገ በቦንጋ ከተማ ይካሄዳል።
የፓናል መድረኩ “የመደመር ትሩፋቶች ለተሻለ ነገ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ሲሆን፣ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የውይይት መነሻ ሃሳቦች ቀርበው ሰፊ ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የመደመር ጉዞ የፓናል መድረኮች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) “መደመር”፣ “የመደመር መንገድ” እና “የመደመር ትውልድ“ በሚሉ ርዕሶች ለንባብ ያበቋቸውን መጽሃፍት መሰረት ያደረጉ ናቸው።
ኢዜአ ከዚህ ቀደም መሰል መድረኮችን በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ጅግጅጋ፣ አሶሳ፣ ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ያካሄደ ሲሆን፣ በነገው እለት በቦንጋ ከተማ የሚካሄደው መድረክም ምዕራፍ ሰባት መሆኑ ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም የተካሄዱ መድረኮች አገር በቀል በሆነው የመደመር እሳቤ ላይ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተብ ክፍሎች እንዲወያዩበት እድል የፈጠሩ ናቸው።