ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገር መከታና ኩራት ከመሆን ባሻገር የልማት አጋርነቱንም በተግባር እያሳየ ነው

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገር አስተማማኝ መከታና የሕዝቦች ኩራት ከመሆን ባሻገር በልማትም አጋርነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ከኅዳር 20 ጀምሮ በተለያዩ መርኃ-ግብሮች በማክበር ላይ ይገኛል፡፡ 

የበዓሉ ማጠቃለያ ታኅሳስ 6 ቀን በልዩ ሁኔታ የሚከናወን መሆኑን የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል። 

በእለቱ በበዓሉ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት የሚሳተፉበት "ጥቁር አንበሳ" የተሰኘ የአየር ላይ ትርዒቶች የሚካሄዱ መሆኑንን ጠቁመዋል።

አየር ኃይሉ ያስገነባቸው የውጊያ መሠረተ-ልማቶች የምርቃት ሥነ-ሥርዓት የሚካሄድ መሆኑንም ገልፀዋል። 


 

በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ አመራሮች፣ አብራሪዎች፣ ቴክኒሻኖች እንዲሁም የበረራ መምህራንና የሌሎችም የምረቃ መርኃ-ግብር የሚከናወን መሆኑንም ጠቁመዋል።

አየር ኃይሉ አካባቢን ለሥራ ምቹ በማድረግ እንዲሁም በልማት ሥራዎች በስፋት በመሳተፍ ያከናወናቸው ሥራዎችም የሚጎበኙ ሲሆን፤ በቅጥር ግቢው በ74 ሄክታር መሬት ላይ የለሙ የተለያዩ አትክልቶችና ሰብሎችም የሚጎበኙ ይሆናል።

በኢትዮጵያ አየር ኃይል የውበትና ልማት መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ምስጋኑ ለገሰ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ተቋሙ የምግብ ፍጆታውን በራሱ ምርት ለመሸፈን በማለም የልማት ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። 

የአየር ኃይሉን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች የተቋሙ ሠራተኞችና የአካባቢው ማኅበረሰብን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀድሞ የአየር ኃይል አባል እና አሁን በልማት ሥራው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ሻለቃ ባሻህ መሐመድ፤ አየር ኃይሉ የሀገር ሉዓላዊነት መከታ ብቻ ሳይሆን የልማትም አርበኛ ሆኗል ብለዋል።

ለዚህም በሰፊው በቅጥር ግቢው ድሮ ያልነበሩ የልማት ሥራዎች አሁን ላይ እርሳቸውን ጨምሮ በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።


 

የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወጣት ፍቃዱ አበበ እና ወርቅነሽ ምትኩ፤ በሚያገኙት ገቢ ለራሳቸውና ቤተሰባቸው ህይወት መቃናት የላቀ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል። 


 

አየር ኃይሉ በቀጣይ የልማት ሥራውን በማስፋት ከሠራተኛው ባሻገር የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ኅዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም የተመሠረተ ተቋም መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም