በዞኑ የተከሰተው ድርቅ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሰቆጣ፤ ታህሳስ 03/2016 (ኢዜአ) ፦ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የተከሰተው ድርቅ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን የዞኑ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት ገለፀ። 

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ምህረት መላኩ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በብሄረሰብ አስተዳደሩ ባለፈው ክረምት በዝናብ መቆራረጥ ችግር በሶስት ወረዳዎች ላይ ድርቅ ተከስቷል። 

በዚህም በሰሃላ፣ ሰየምት፣ አበርገሌና ዝቋላ ወረዳዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ገልጸዋል። 

በአካባቢው ድርቁ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስም እስካሁን 14 ሺህ 782 ኩንታል የምግብ እህል በማቅረብ ለ112 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች የመጀመሪያ ዙር ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

የክልልና የፌደራል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽኖች፣ ንጋት ኮርፖሬትና ሌሎች የበጎ አድራጎት ማህበራት በዞኑ የድርቅ አደጋው የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት በተለያዩ ተግባራት እየደገፉ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

ከምግብ እህል በተጨማሪም በተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኩል 96 ነጥብ 8 ሚሊዮን ጥሬ ገንዘብ ለአንድ አባወራ ሰባት ሺህ ብር የቀጥታ ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል። 

አሁን ላይም በመጀመሪያው ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ ላልደረሳቸው ከ68 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ እህል ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። 

ድርቁ በቤት እንስሳት ላይ የመኖ እጥረት መፍጠሩን ጠቁመው፤ ችግሩ እንዳይባባስ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። 

በሰሃላ ሰየምት ወረዳ የ09 አቅኝ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አማኑዔል አስፋው በበኩላቸው፤  ከበጎ ፈቃደኞች በተደረገላቸው የ14 ሺህ ብር ድጋፍ የምግብ እህል በመግዛት ቤተሰቦቻቸውን መመገብ ችለዋል።   

ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሉቀን አበበ በበኩላቸው፤ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው በተጨማሪ በእንስሳት ላይም ችግር እየደረሰ ነው። 

መንግስት የአንድ ወር ቀለብ የምግብ እህል እንዳቀረበላቸውም ጠቁመዋል።  

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዝናብ አጠር ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ ሲሆን፤ በተለያዩ ዘመናት ለድርቅ እንደሚጋለጥ  መረጃዎች ያመላክታሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም