በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የገጠሩን ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የገጠሩን ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው
ሐረር ፤ ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ) ፦ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የገጠሩን ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሐረርጌ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሚደጋ ወረዳ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቻቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታምሩ ገደፋ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ሚኒስቴሩ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የገጠሩን ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በተለይ በቆላማ አካባቢዎች ለህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማዳረስና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንን ለማሳደግ የገነባቻቸው ፕሮጀክቶች ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሐረርጌ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት የኮንስትራክሽንና ኮንትራት አስተዳደር ዩኒት ኃላፊ አቶ አበበ ለገሰ እንደገለጹት በሮባ ቀበሌ የተገነቡት የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከ1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር በላይ የውሃ መስመር የተዘረጋላቸው ናቸው።
ግንባታቸው በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች አራት የውሃ ማደያዎች እና 100 ሜትር ኪዩብ ውሃ መያዝ የሚችል ማጠራቀሚያ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ለፕሮጀክቶቹ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የኃይል ማመንጫ ግንባታ መከናወኑን የገለጹት አቶ አበበ፣ ፕሮጀክቶቹ ከ6 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል።
አቶ አበበ እንደገለጹት ድርጅቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት በዞኑ 8 ወረዳዎች ከ292 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ የውሃ ፕሮጀክቶችን አስገንብቷል።
በዚህም ከ42 ሺህ በላይ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደምታጠናክርም አስታውቀዋል፡፡
የካቶሊክ ዕርዳታ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ዘመዴ አበበ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ የማህበረሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
በተለይም እንደ ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የንጹህ መጠጥ ውሃ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ድርጅቱ የጀመረውን የልማት ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።
የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፈዲላ ዳውድ በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያኗ የገጠሩን ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለልና ተጠቃሚ ለማድረግ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ፕሮጀክቱ በአስቸጋሪ መልከዓ ምድር መገንባቱ፣ በታቀደው ጊዜና በጀት መጠናቀቁ ለቀጣይ መሰል ሥራዎች ልምድ የተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የወረዳው ነዋሪዎች ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል።
በሚደጋ ወረዳ የሮባ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ራህዬ አደም በሰጡት አስተያየት በቀበሌው ለዓመታት ሲያቀርቡት የነበረው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥያቄ አሁን ምላሽ ማግኘቱን ገልጸዋል።
"ከኩሬና ከወራጅ ወንዝ ውሃ ፍለጋ እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት መንከራተት ቀርቶልናል፤ ችግራችን ተፈቶልናል፤ የሰራልንን አካል እናመሰግናለን" ብለዋል፡፡
"በአካባቢያቸው የነበረው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ልጆቻችን ትምህርት እንዳይከታተሉ እንቅፋት ፈጥሮብን ቆይቷል፤ አሁን ግን ችግራችን መፍትሄ በማግኘቱ ተደስቼያለሁ" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሃዲያ ሳኒ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው።
"አሁን ላይ ችግሩ መፈታቱ ለእኛም፣ ለልጆቻችንም ለሁሉም ማህበረሰብ ትልቅ እፎይታ ሰጥቷል" ብለዋል፡፡