ምክር ቤቱ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች መጠናከር የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል - አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች መጠናከር የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል - አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ) ፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአምራች ኢንተርፕራይዞች መጠናከር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የእኛ ምርት አምራች ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር "ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ኃሳብ ዛሬ ተጀምሯል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ወደ ኃብት ሊቀየሩ የሚችሉ የበርካታ የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት መሆኗን ጠቁመዋል።
የተፈጥሮ ፀጋ ወደ ኃብት ለመቀየር የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ገበያና ፈጠራ እንዲሁም አገራዊ ፍላጎትና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን አመዛዝኖ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።
ከዚህ አንጻር መንግሥት ለአምራች ኢንተርፕራይዞች በሰጠው ትኩረት በርካታ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት መቻሉንም ነው ያመላከቱት።
በኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍና ማበረታታት የበለፀገችና ታላቋን ኢትዮጵያ የመገንባት ተጋድሎ መሆኑን ገልፀዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአምራች ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የሕግ ማሻሻያዎችን ያደርጋልም ብለዋል።
የአምራች ኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም ነው የጠቆሙት።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው፤ መንግሥት በአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱ ከለያቸው አምስት የኢኮኖሚ የትኩረት መስኮች የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አንዱ ነው ብለዋል።
በዚህም የአሠራር ማሻሻያዎችን በማድረግ የብድር አቅርቦት፣ የመሠረተ-ልማት ግንባታና የገበያ ትስስር በመፍጠር ዘርፉን እየደገፈ መሆኑን ገልፀዋል።
በአሥር ዓመት የልማት ዕቅዱ መጨረሻ ወደ ውጭ ከሚላክ ምርት ከ9 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዷል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከ370 በላይ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ በማስገባት የአምራች ኢንተርፕራይዞችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ ጨምሮ ከውጭ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ከ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ ማዳን እንደተቻለ ጠቅሰዋል።
ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ይቆያል።