ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እየተመናመኑ ያሉ የብዝኃ ሕይወት ኃብቶችን የመጠበቅ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል   

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ እየተመናመኑ ያሉ የብዝኃ ሕይወት ኃብቶችን እንዳይጠፉ የማድረግ ሥራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ገለፀ። 

ብዝኃ ሕይወት ሁሉንም ሥነ-ሕይወታዊ ኃብቶች፣ እፅዋት፣ እንስሳትና ደቂቅ ዘአካላት እንዲሁም በውስጣቸው የያዟቸው ዘረ-መሎችና እነዚህ የሚፈጥሯቸውን ውህዶች የሚያካትት ነው። 

ኢትዮጵያም ከፍተኛ የብዝኃ ሕይወት ኃብት ካላቸው አገራት መካከል አንዷ ናት።

አሁን ላይ አገሪቱ ከ6 ሺህ በላይ የእፅዋት ኃብቶች ያላት ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 600 ወይም 10 በመቶ የሚሆኑት በአገሪቱ ብቻ የሚገኙ ናቸው። 

ጎን ለጎንም የወፍ ዝርያዎችን ጨምሮ በየብስና በውኃ አካላት ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ዓይነት ዝርያ ያላቸው በርካታ እንስሳት በኢትዮጵያ ይገኛሉ። 

ይሁንና የየብስና የውኃማ አካላት አካባቢ መለወጥ ለእነዚህ ብዝኃ ሕይወት ኃብቶች ሥጋት እየሆነ መምጣቱን ነው የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዮ የሚናገሩት።  

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ብክለትና ዘለቄታዊ ያልሆነ የተፈጥሮ ኃብት አጠቃቀም  ለብዝኃ ሕይወት ኃብቶች መመናመን ምክንያት መሆናቸውን ገልፀዋል።

የሕዝብ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ ደን ወደ እርሻ መሬትነት መቀየር እንዲሁም መጤ ወራሪ አረሞች ነባር አገር በቀል ዝርያዎች የሚበቅሉበትን ሥፍራ መያዝም ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል።  

ይህንንም ተከትሎ ወይራ፣ ዝግባ፣ ቀረሮ፣ ዋንዛ፣ ጥቁር እንጨትና ኮሶ እየተመናመኑ ካሉ የእፅዋት ብዝኃ ሕይወት ዝርያዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል። 

ዝርያዎቹ አንዴ ከጠፉ መልሰው የማይገኙ በመሆናቸው ኢንስቲትዩቱ ዝርያዎቹን የማራባትና የማብዛት ሥራ በልዩ ትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

ከእነዚህም በተጨማሪ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸውና በኢትዮጵያ ብቻ ያሉ የእፅዋትና እንስሳት ብዝኃ ሕይወት ዝርያዎችን የመጠበቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።  

በዚህም የቀረሮ የእጽዋት ዝርያ የማብዛት ሥራ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የተመናመኑ የዳልጋ ከብቶች ወደ ነበሩበት የመመለስ ሥራም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

በተመሳሳይ "የሸኮ ዳልጋ ከብት" እየተባለ የሚጠራውን ዝርያ የማብዛት እንዲሁም በጣና ኃይቅ የዓሳ ዝርያዎች ላይ ያለውን መመናመን ለመቀልበስም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።  

ጥብቅ አካባቢዎችን የማስፋት፣ የእፅዋት አፀድ ጥበቃ፣ የዘረመልና የማኅበረሰብ የዘር ባንኮችን በየአካባቢው የማስፋት ተግባርም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብርም የብዝኃ ሕይወትን ከመጠበቅና ከማስቀጠል አኳያ ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን አመልክተዋል።

የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ላይ አበክረው እንዲሰሩና ቅንጅታዊ አሠራራቸውን እንዲያጠናክሩ ዶክተር መለሰ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ያሏትን የብዝኃ ሕይወት የመጠበቅ ተልዕኮ የተሰጠው የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩትም ኃብቶቹን የማንበር (የመጠበቅ)፣ ዘለቄታዊ አጠቃቀምና ፍትሃዊ የጥቅም ተጋሪነት ላይ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም