ለኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ የሆኑ ብቁ ባለሙያዎችን እያፈራን በመሆኑ ሁሌም ክብርና ኩራት ይሰማናል-የአካዳሚው መምህራን - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ የሆኑ ብቁ ባለሙያዎችን እያፈራን በመሆኑ ሁሌም ክብርና ኩራት ይሰማናል-የአካዳሚው መምህራን
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ)፦ ለኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብ የሆኑና የላቀ የሙያ ብቃት ያላቸውን አብራሪና ቴክኒሻኖች እያፈራን በመሆኑ ሁሌም ክብርና ኩራት ይሰማናል ሲሉ የአየር ኃይል አካዳሚ አመራርና መምህራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ ዓለም አቀፍ የብቃት መስፈርትን ያሟሉና የዘመኑን ቴክኖሎጂ የዋጁ አብራሪዎችንና ቴክኒሺያኖችን እያፈራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከተመሠረተ 88 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ መንግሥት ለፀጥታ ተቋማት በሰጠው ልዩ የፖሊሲና የበጀት ትኩረት ተጨባጭ ለውጦችን አካሂዷል።
ለአብነትም በሰው ኃብት ግንባታ ዘርፍ የአየር ክልሉን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስጠብቁና የዘመኑን ቴክኖሎጂ በብቃት የሚመሩ አብራሪዎችንና የጥገና ባለሙያዎችን እያሰለጠነ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ ዲን ኮሎኔል ለማ ማሞ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ ስመ-ጥር አብራሪዎችንና ቴክኒሺያኖችን በማፍራት የአየር ኃይሉ የሰው ኃብት ግንባታ የጀርባ አጥንት ሆኖ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
ከለውጡ ወዲህ የአየር ኃይሉ የሰው ኃይል አቅም ግንባታና የሙያ ሥልጠናን በመገንባት ተልዕኮውን በላቀ ብቃት እየተወጣ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
አየር ኃይሉ የአየር ክልሉን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠብቅ አብራሪዎችንና ቴክኒሺያኖችን ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የዋጁ እንዲሆን ሌት ተቀን እያሰለጠነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ በላይ የሚያኮራ ነገር የለም ያሉት ኮሎኔል ለማ፤ አየር ኃይሉ የኢትዮጵያ ሰማይ አስተማማኝ ዘብ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
አየር ኃይሉን በ1981 የተቀላቀሉት ማስተር ቴክኒሺያን ግርማ ሮባ፤ የሱ 27፣ የሚግ 21 እና ሌሎችም የጦር ጄቶች ቴክኒሺያን ሆነው ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፤ ላለፉት 14 ዓመታት ደግሞ የአየር ኃይል አካዳሚ መምህር ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ።
ማስተር ቴክኒሺያን ግርማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአየር ኃይሉ አባል መሆን ኩራትም ክብርም መሆኑን ይናገራሉ።
በተለይም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋነኛ ትኩረት የሆነው የሰው ኃይል ግንባታ ላይ በመሰማራት፤ ስመ-ጥር አብራሪዎችንና የጥገና ባለሙያዎችን እያፈሩ መሆኑ ደስታው ወደር እንደሌለው ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያም እኔም የምንኖረው አየር ኃይሉ ሲኖር ነው" ያሉት ማስተር ቴክኒሺያን ግርማ በቀጣይም ብቁ አብራሪዎችና ቴክኒሺያን ለማፍራት በዕድሜያቸው ሁሉ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለሀገርና ሕዝብ ደኅንነት የጀርባ አጥንት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከውጭ የሚመጣና ከውስጥ የሚፈትኑ ጠላቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ በመመከት ሀገርን ከእነክብሯ ማስቀጠሉንም ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ የቴክኒሺያንና የአብራሪዎቹ ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ አውሮፕላንን ጠግኖ ሀገር ልታወጣው የምትችለውን የውጭ ምንዛሬ የሚያድኑ ወጣት ባለሙያዎችን ማፍራት ስሜቱ ወደር የለውም ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በ2004 ዓ.ም ተቀላቅለው ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ የአቪዬሸን ኤሌክትሮኒክስ ክፍል ኃላፊ የሆኑት መቶ አለቃ ረቢራ እንድሪስ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከለውጡ ወዲህ ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂ ተሟልቶለት እየሠራ ነው ብለዋል።
"ሀገሬ ሳይኖራት ነው ያስተማረችኝ" ያሉት መቶ አለቃ ረቢራ፤ በአሁኑ ወቅት ለሀገራቸው ዘብ የሚቆሙ የአየር ኃይል አባላትን ለማፍራት በተሰማሩበት ሙያ በማገልገላቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።
አመራሮቹ አየር ኃይሉ የአፍሪካ አየር ኃይል መሪ ለመሆን የያዘውን ርዕይ ለማሳካት አካዳሚው የአፍሪካና ሌሎች ሀገራት የአየር ኃይል የልህቀት ማዕከል ሆኖ እንዲሰራ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።
የሥልጠና ሥርዓተ-ትምህርቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት አመራሮቹ፤ ማሰልጠኛ አውሮፕላኖችና ሌሎች መሳሪያዎችም ዘመኑ የደረሰባቸው ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገሪቱ የሰማይ ዘብ መሆኑን በመገንዘብ ተቋሙን ተቀላቅሎ ሀገሩን እንዲያገለግልም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማጠቃለያ መርሃ-ግብር በመጪው ታኅሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።