ቀጥታ፡

የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አከባበር በብዝኃነት ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና የጋራ እሴቶች እየተገነቡበት ያለ መድረክ ሆኗል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 03/2016 (ኢዜአ)፦ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አከባበር በብዝኃነት ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና የጋራ እሴቶች እየተገነቡበት ያለ መድረክ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ።

የ18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ከኅዳር 25 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በልዩ ልዩ ደማቅ ሥነ-ሥርዓቶች ተከብሯል።

በእያንዳንዱ እለት የወንድማማችነት፣ የብዝኃነት፣ የአብሮነት፣ የመደመርና የኢትዮጵያ ቀናት በሚሉ መሪ ሃሳቦች መከበሩም ይታወቃል።

የበዓሉ አከባበር አንዱ የሌላኛው አለኝታ፣ ጌጥና ውበት መሆኑን የተመለከትንበትና ብዝኃነት የሀገር የጋራ እሴትና ኃብት መሆኑ በተግባር የታየበት ሆኖ አልፏል።

የበዓሉን አከባበርና አጠቃላይ ሀገራዊ ፋይዳውን በሚመለከት ኢዜአ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ተረፈ በዳዳ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው በጅግጅጋ የተከበረው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በብዝኃነት ውስጥ ሀገራዊ አንድነት ጎልቶ የታየበት መሆኑን ተናግረዋል። 

የበዓሉ አከባበር በብዝኃነት ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትና የጋራ እሴቶች የተስተዋሉበት የኢትዮጵያውያን የብዝኃነት፣ የአብሮነትና የአንድነት መድረክ ስለመሆኑም ገልፀዋል።

በሁነቱ የባህል፣ የቋንቋ፣ የአልባሳትና የማንነት መገለጫዎች፣ ጥልቅ እሴቶች ጎልተው የወጡበትና የእርስ በርስ መተዋወቂያ ልዩ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም እነዚህን ጥልቅ እሴቶች የጋራ ኃብቶች በማድረግ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ የሁላችንም ቀጣይ ሥራዎች ሊሆኑ ይገባል ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ተነግሮ የማያልቅ ታሪክና ተዝቆ የማያልቅ ዕምቅ ኃብት ያላትና ለሁላችንም የምትበቃ ሀገር በመሆኗ በጋራ ለመገንባት እንዘጋጅ በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አከባበር ከኢትዮጵያውያን የአብሮነትና አንድነት ማሳያነቱ ባለፈ ኢትዮጵያን ለዓለም የምናስተዋውቅበት መድረክ ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። 

በቀጣይ ዓመትም 19ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ በላቀ ዝግጅት የሚከበር ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም