ኢትዮጵያ ለ120 የደቡብ ሱዳን ዜጎች ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጠች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለ120 የደቡብ ሱዳን ዜጎች ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጠች
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 3/2016 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ለ120 የደቡብ ሱዳን ዜጎች ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጠች፡፡
ነጻ የትምህርት ዕድሉ በቴክኒክና ሙያ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ጁባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለተማሪዎቹ የሽኝት ፕሮግራም ማዘጋጀቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነቢል ማህዲ የነፃ የትምህርት ዕድሉን ላገኙ ተማሪዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግስት በሁለቱ ሀገራት መካከል በአቅም ግንባታ እና በሰው ልማት ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የደቡብ ሱዳን የከፍተኛ ትምህርት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምክትል ሚኒስትር ዶክተር አዲል አትናኑሲዮ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት በትምህርትና በአቅም ግንባታ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።