ቀጥታ፡

የትምህርት ሥርአቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት በቅንጅት እየተሰራ ነው

ድሬደዋ፤ ታህሳስ 2/2016 (ኢዜአ) ፡-በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ ትምህርቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተወጣጡ  ምሁራን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የትምህርት አሰጣጥና አዘገጃጀት ላይ የተሰጣቸውን ስልጠና አጠናቀዋል።

ለስምንት ወራት ስልጠናቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁት  ምሁራን ከተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ናቸው። 

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ በተካሄደው የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተው የምስክር ወረቀት የሰጡት በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ኤባ ሚጂና እንደተናገሩት፤ የትምህርት ሥርዓቱ ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ዘመን ጋር ካልተዋሃደ በዘርፉ የሚፈለገውን ለውጥና አገራዊ ዕድገትን ማምጣት አይቻልም።


 

ይህንን መሠረት በማድረግ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ ትምህርቶችን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን "መምህራንን የማብቃትና አቅማቸውን የመገንባት ሥራ በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል" ብለዋል።

እንደ ዶክተር ኤባ ገለጻ፣ የትምህርት ስርዓቱን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሂደት ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባለፈ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚያስችል ነው።

"ያለ ቴክኖሎጂ እገዛ የትኛውንም አገራዊ ዕድገት ማሳካት አይቻልም" ያሉት ዶክተር ኤባ፣ ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ እንደአገር ውጤታማ ሥራ ለመስራት ወደ ዘርፉ መገባቱን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡባህ አደም በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ያለዲጂታል ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፍን ማበልፀግም ሆነ ተወዳዳሪና በክህሎት የታጠቀ ባለሙያን ማፍራት ከባድ ነው።

በመሆኑም በአገራችንን የትምህርት ዘርፍ ላይ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል የዲጂታል ቴክኖሎጂ መጀመሩ "በኦንላይን የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው" ብለዋል።

"በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እየተገነባ ያለው ስቱዲዮ ለምስራቅ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ማዕከል ሆኖ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል" ሲሉም ገልጸዋል።

"በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በዲጂታላይዜሽን የትምህርት አሰጣጥ፣ አዘገጃጀትና ተያያዥነት ባላቸው መሠረታዊያን ላይ ከ35 ሺህ በላይ መምህራንን እና ከ800 ሺህ በላይ ተማሪዎች አስፈላጊውን ስልጠና ይሰጣል" ያሉት ደግሞ ፕሮጀክቱን የሚደግፈው የካናዳው የማስተር ካርድ ዓለምአቀፍ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ያለው ናቸው።

እንደእሳቸው ገለጻ የዲጂታል ቴክኖሎጂ በትምህርት ስርዓት ውስጥ በተቀናጀ መንገድ መካተቱ የትምህርትን ጥራት፣ ተደራሽነትና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

ይህ አሠራር በኮቪድ ወረርሽኝና እና መሠል ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ወቅት የመማር ማስተማር ሥራው እንዳይቋረጥ ማድረጉን አስታውሰዋል።

አቶ ሳሙኤል  እንደገለፁት፤ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማስተማር ዘዴን በሙሉ አቅም በቁርጠኝነት መተግበር ከተቻለ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ላይ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያስችላል።

ከዚህ በተጨማሪ አገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ በተማረ የሰው ኃይል ተወዳዳሪና ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም አመልክተዋል።

ለአምስት ዓመታት የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት የትምህርት ሚኒስቴር ከማስተር ካርድ ዓለምአቀፍ ፋውንዴሽን፣ ከአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ እና ከኢ.ሺ አገር አቀፍ አማካሪ ድርጅት ጋር በመተባበር በሃምሳ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚተገበር መሆኑ ታውቋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም