በኢትዮጵያ አበረታች መድኃኒትን ለመከላከል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ እንዲዋቀር ጥያቄ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ አበረታች መድኃኒትን ለመከላከል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ እንዲዋቀር ጥያቄ ቀረበ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 2/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አበረታች መድኃኒትን ለመከላከል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ እንዲዋቀር ጥያቄ አቀረበ።
የፌዴሬሽኑ የአትሌቲክስ ሕክምና ኃላፊ ዶክተር አያሌው ጥላሁን፤ በጉዳዩ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የአበረታች መድኃኒት ቅመም ጉዳይ በየጊዜው እየተባባሰና አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
የስፖርቱን ዘርፍ የሚጎዳውን ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር ለመግታት ደግሞ ትብብርና የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል።
ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ እንዲዋቀር ፌዴሬሽኑ ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረቡን ዶክተር አያሌው ገልፀዋል።
ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የፊታችን ሐሙስ በጉዳዩ ዙሪያ የሚመክር ጉባዔ በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዓለም የስፖርት ችግር የሆነው አበረታች ቅመም ለኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርትም አሁን ላይ ስጋት እየሆነ መጥቷል ያሉት ኃላፊው፤ በተለይም አትሌቶችና የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ስለ ጉዳዩ ሰፊ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም በዚህ ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግና አትሌቶችን ከዚህ ችግር ነፃ ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ኮሚቴ ማዋቀር ማስፈለጉን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ከአበረታች ቅመም ጋር በተያያዘ ስምንት አትሌቶች ቅጣት የተላለፈባቸው ሲሆን፤ ሁለት አትሌቶችም በጊዜያዊነት መታገዳቸው ይታወቃል።