የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ከነበረበት 2 ቢሊየን ብር ወደ 11 ቢሊየን ብር አደገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ከነበረበት 2 ቢሊየን ብር ወደ 11 ቢሊየን ብር አደገ
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 2/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ባለፉት ሦሰት ዓመታት ከነበረበት 2 ቢሊየን ብር ወደ 11 ቢሊየን ብር ማደጉ ተገለጸ።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በሊዝ ፋይናንሲንግ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ከነበረበት 2 ቢሊየን ብር ወደ 11 ቢሊየን ብር ማደግ መቻሉንም ባንኩ ገልጿል።
ባንኩ በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ደንበኞቹ 15 ትራክተርና 10 ኮምባይን ሀርቨስተር እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ ለተሰማሩ ደንበኞቹ 14 ኤክስካቫተር በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት አቅርቧል።
የኮምባይን ሀርቨስት መሳሪያዎቹ 72 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመቱ ሲሆን፤ ትራክተሮቹ ከ43 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም ኤክስካቫተሮቹ ከ87 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ መሆናቸውንም ባንኩ አስታውቋል።
በርክክቡ ወቅት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው፤ ባንኩ ላለፉት አምስት ዓመታት የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን አከናውኖ በኢትዮጵያ ካሉ ባንኮች ሁለተኛውን ካፒታል ማስመዝገብ ችሏል ብለዋል።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ አገልግሎትና ሌሎችም ዘርፎች ወደ ሥራ ለተሰማሩ ዜጎች የሚያደርገው ድጋፍ በየጊዜው እድገት እያሳየ መሆኑንም አንስተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከያዘው 51 ቢሊየን ብር ውስጥ 15 ቢሊየን ብር ለግብርና ዘርፉ የተመደበ መሆኑንም ገልፀዋል።
በግብርናው ዘርፍ የተደረገው የመሳሪያ ርክክብ የግብርና ሜካናይዜሽንን በማጠናከር የምርት ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት ለመቆጠብ አስተዋፅዖ የሚኖረው መሆኑንም አስረድተዋል።
የግብርና ዘርፉን ማዘመንና ምርታማነቱን ማሳደግ ኢንዱስትሪዎች በቂ ጥሬ ዕቃ አግኝተው በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ እገዛ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በማዕድን ዘርፉ የተሰጡ መሳሪያዎችም አገሪቱ በዘርፉ ያላትን ሰፊ ዕድል እንድትጠቀም የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ በሊዝ ፋይናንሲንግ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ባንኩ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከነበረበት 2 ቢሊየን ብር ወደ 11 ቢሊየን ብር ማደጉንም ጠቅሰዋል።
ባንኩ ለ486 ደንበኞች ከ580 በላይ ለግብርና አገልግሎት የሚውሉ መሳሪያዎችንና ከ100 በላይ የሚሆኑ ለማዕድን ዘርፉ የሚጠቅሙ ኤክስካቫተሮችን ለደንበኞቹ ማቅረቡንም ተናግረዋል።
አቶ እንዳለ መኩሪያ እና አቶ እንዳለ ቡታ፤ የተረከቧቸው መሳሪያዎች ሥራቸውን የሚያዘምኑ ከመሆናቸው ባሻገር ገቢ ምርቶችን ለመተካትና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማሳደግ የሚያስችሉ መሆኑን ገልፀዋል።
ሌላኛው ተረካቢ አቶ ዳንኤል ወልደሰንበት፤ የተረከቡት ኤክስካቫተር በተሰማሩበት የማዕድን ዘርፉ የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።