ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት መከታ ከመሆኑም ባለፈ ችግሮች ሲያጋጥሙ ፈጥኖ በመድረስ የዜጎችን ነፍስ በማዳን ባለውለታ ነው

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 2/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት መከታ ከመሆኑም ባለፈ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ፈጥኖ በመድረስ የዜጎችን ነፍስ በማዳን ባለውለታ መሆኑን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከጥንት እስካሁንም የኢትዮጵያ አየር ክልል አስተማማኝ ዘብና የሀገር ሉዓላዊነት መከታ በመሆን ትልቅ ስምና ዝና ያለው ተቋም መሆኑ ይታወቃል። 

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተመሠረተበት ኅዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም ጀምሮ በየዘመኑ በርካታ ጀግኖች ለሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት ደማቅ አሻራቸውን እያኖሩበት እስካሁንም ዘልቋል። 

በዚህም መነሻነት ዘንድሮ 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ከኅዳር 20 ቀን ጀምሮ በተለያዩ መርኃ-ግብሮች በማክበር ላይ ይገኛል።

አየር ኃይሉ ለሀገር ዳር ድንበር ዘብ በመሆን ከጫፍ ጫፍ ከመብረር ባለፈ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲያጋጥሙም ፈጥኖ በመድረስ የዜጎችን ህይወት ይታደጋል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተር ታዬ ጌታቸው፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት ዘብ ከመሆኑ ባለፈ በችግር ጊዜ የዜጎች ፈጥኖ ደራሽና አለኝታ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በጎርፍ የተከበቡ ዜጎችን ከአደጋ በማውጣትና በፍጥነት ሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽ በማድረግ የወገኖችን ህይወት በመታደግ የማይተካ ሚናውን እየተወጣ እስካሁንም ዘልቋል ብለዋል።

በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ባጋጠሙ ጊዜ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሄሊኮፕተሮችን በፍጥነት በማሰማራት ለሰዎች የደረሰበት አጋጣሚ ብዙ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አየር ኃይሉ ከአየር ድጋፍ በተጨማሪም ባለሙያዎችን በመመደብ ለአደጋ ምላሽ በመስጠት የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ቀላል አለመሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ታኅሳስ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ መግለጻቸው ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም