ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለድኅረ-ምርት ስብሰባ አመቺ የአየር ሁኔታ ይኖራል

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 2/2016(ኢዜአ)፡-በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የመኸር ሰብል አምራች በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ለድኅረ-ምርት ስብሰባ አመቺ የሚሆን የአየር ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ  ኢንስቲትዩት አስታወቀ።   

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ የመኸር ሰብል አምራች ለሆኑ አካባቢዎች ለድኅረ-ሰብል ስብሰባ አመቺ ነው።

አርሶ አደሩ አመቺ የአየር ሁኔታን በመጠቀም ሰብሉን  በፍጥነት እንዲሰበስብ ትንበያው አመልክቷል።

በሌላ በኩል ከደረቃማ የእርጥበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ በሰሜን፣ በምስራቅና በደቡብ ደጋማ ሥፍራዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ቀጣይነት የሚኖረው መሆኑን ጠቁሟል። 

ይህም እድገታቸውን  ላልጨረሱ፣ ለቋሚ ተክሎችና በመስኖ በመታገዝ በሚለሙ ሰብሎች እና የፍራፍሬ ተክሎች ላይ አሉታዊ ጎን ሊኖረው ስለሚችል አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት  ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክቷል።

በደቡብ እና በምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚጠበቀው ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው እርጥበት ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች ለቋሚ ተክሎች እንዲሁም ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆኑት ደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚያከናውኑት የጥምር ግብርና ሥራ የውሃ ፍላጎት መሟላት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ይጠበቃል። 

በተጨማሪም የሚገኘው እርጥበት በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ጎን ይኖረዋል። 

በሰሜን እና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት ስለሚኖር፣ በደረሱና እየተሰበሰቡ በሚገኙ አዝርዕቶች ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ትንበያው አብራርቷል።

በሌላ በኩል ለዝናብ መፈጠር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሜቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ከሳምንቱ አጋማሽ በኋላ የተሻለ ጥንካሬ ይኖራቸዋል።

ስለሆነም በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብና ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

ይህም በደረሱና እየተሰበሰቡ በሚገኙ አዝርዕቶች ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ትንበያው አመልክቷል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም