ቀጥታ፡

በመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ በተደረጉ የሪፎርም ስራዎች የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ ተችሏል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2016 (ኢዜአ)፡- በመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ በተደረጉ የሪፎርም ስራዎች የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ እንደተቻለ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው የገንዘብ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የሶስት ወራት አፈጻጸምን በተመለከተ በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ ነው።


 

በመድረኩ እንደተጠቀሰው በሩብ ዓመቱ በጥቅል ሀገራዊ ምርት፣ በነፍስ ወከፍ ገቢ ረገድና ሌሎችም የኢኮኖሚ መሻሻል አመላካቾች ላይ ዕድገት ታይቷል።

በሩብ ዓመቱ የመንግስት ወጪ 123 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ያጋጠመ የ34 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት በሀገር ውስጥ ምንጮች መሸፈኑም ተጠቅሷል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የመንግስት የልማት ድርጅቶች በሆኑት በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በኢትዮ-ቴሌኮም እና በመሳሰሉ የመንግስት የልማት ተቋማት ላይ በተደረጉ የሪፎርም ስራዎች የገቢ አቅማቸውን ማሳደግ ተችሏል።

በተጨማሪም ከልማት አጋሮች ጋር በቅንጅት በመሰራቱ የውጭ ሃብት ግኝት ከማሳደግ ባሻገር የበጀት ጉድለትን መሽፈን መቻሉን ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።

ታክስ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የፋይናንስ አስተዳደሩን ማጠናከር እና ማዘመን እንደሚገባ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የመንግስትን የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች በተመለከተም የገቢ አሰባሰብን ለማሳደግ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመሆን በቅንጅት እንደሚስራ አሰረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ተግባራዊ በሚደረገበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስቴር ድጋፍ እንደሚያደርግ መናገራቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም