የኢትዮጵያና ኳታር የንግድና ኢንቨስትመንት የምክክር መድረክ በኳታር ዶሃ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ኳታር የንግድና ኢንቨስትመንት የምክክር መድረክ በኳታር ዶሃ ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2016 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያና በኳታር መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የንግድና ኢንቨስትመንት የምክክር መድረክ በኳታር ዶሃ ተካሂዷል።
መድረኩ በዋናነት በአትክልትና አበባ ዘርፍ ልማት፣ በግብርና ምርቶች ንግድ እና በቱሪዝም ላይ ያለውን የሁለቱን ሀገራት ትብብር በማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ የኳታር የንግድ ተቋማት በኢትዮጵያ መዕዋለንዋያቸውን በማፍሰስ በግብርናው ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ አክለውም፣ መድረኩ የቱሪስት መስህቦች በኳታር እና በአለም አቀፍ ገበያ እንዲተዋወቁና የኢትዮጵያ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ገበያ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የግብርና ምርቶቿን የምታሳይበት ርዕየ መስኮትንም መርቀው ከፍተዋል።
በኳታር የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፈይሰል አሊ በበኩላቸው፣ በግብርና፣ አየር በረራ፣ ቱሪዝም እና የሀይል ልማት ዘርፎች ሁለቱ ሀገራት ንግድና ኢንቨስትመንትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።