አየር መንገዱ አዲሱን " የኤርፖርት ሲቲ" ግንባታ በአራት ዓመታት ለማጠናቀቅ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ አዲሱን " የኤርፖርት ሲቲ" ግንባታ በአራት ዓመታት ለማጠናቀቅ እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየጨመረ የመጣውን የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት የጀመረውን " የኤርፖርት ሲቲ" ግንባታ በአራት ዓመታት ለማጠናቀቅ እየሰራ ነው።
በአሁን ጊዜ የቢሾፍቱ "ኤርፖርት ሲቲ" ግንባታ ለማስጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለማ ያደቻ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ አየር መንገዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 በዓለም ስመ-ጥር ከሆኑ 20 አየር መንገዶች አንዱ የመሆን ራዕይ ይዞ እየሰራ ነው ብለዋል።
ይህን ራዕይ ለማሳካትም አየር መንገዱ ጠንካራ የሥራ ባህል እንዳለውና አዳዲስ አሠራሮችን በመተግበር ዓመታዊ ዕድገቱን በአማካኝ ከ20 እስከ 25 በመቶ ማድረስ መቻሉንም አንስተዋል።
አየር መንገዱ በተያዘው ዓመት 84 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ያቀደ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ የ25 አውሮፕላኖች ግዥ በመፈፀሙ ለመረከብ እየጠበቀ መሆኑን አንስተዋል።
እንደ አቶ ለማ ገለፃ፤ የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አሁን ባለው ሁኔታ በዓመት 25 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም አለው ብለዋል።
በ2015 ዓ.ም. 14 ሚሊየን መንገደኞችን ያስተናገደ ሲሆን፤ በተያዘው ዓመት ደግሞ 18 ሚሊየን መንገደኞችን ለማስተናገድ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
አየር መንገዱ በዘርፉ እያስመዘገበ ያለውን ፈጣን እድገት ተከትሎ የቦሌ አየር ማረፊያ ከሦስት ዓመት በኋላ ከደንበኞች ብዛት አንፃር የማስተናገድ አቅሙ ሊፈተን ይችላል ብለዋል።
አየር መንገዱ እያስመዘገበ ያለውን ፈጣን ዕድገት ለማስተናገድም በቢሾፍቱ ከተማ ተለዋጭ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያና የኤርፖርት ከተማ ለመገንባት ከአዋጭነት ጥናት ጀምሮ በቂ ዝግጅቶች እያደረገ ነው ብለዋል።
"የኤርፖርት ሲቲ" ፕሮጀክት በአጠቃላይ 5 ቢሊየን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን፤ በዓመት 100 ሚሊየን መንገደኞችን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል።
በኦሮሚያ ክልል ከቢሾፍቱ ከተማ ጥቂት ወጣ ባለ ሥፍራ ላይ እንደሚገነባ የተገለጸው ይህ ፕሮጀክት፤ ዘመናዊ ሆቴሎች፣ ከቀረጥ ነፃ የግብይት ሥፍራና የካርጎ ሎጂስቲክስ ማዕከል እንደሚኖረውም ነው የተጠቆመው፡፡
በአሁን ጊዜ ግንባታውን መጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የተናገሩት አቶ ለማ፤ የአዋጭነት ጥናት በማጠናቀቅ ዓለም አቀፍ ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ለማስጀመር የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
እንደ አቶ ለማ ገለፃ፤ አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ጂኦ-ፖለቲካ መለዋወጥ ምክንያት የሚገጥሙትን ችግሮችን እየፈታ ዕድገቱን ማስቀጠል ችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን እያሳየ ያለውን ፈጣን ዕድገትና ትርፋማነት ግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የአየር መንገዱን ካፒታል ከነበረበት 100 ቢሊየን ብር ወደ 300 ቢሊየን ብር ከፍ እንዲል አድርጓል።