ቀጥታ፡

ኮፕ 28 ዛሬ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2016(ኢዜአ)፦ላለፉት 12 ቀናት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ ሲካሄድ የቆየው 28ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ /ኮፕ 28/ ዛሬ ይጠናቀቃል። 

በጉባዔው ላይ በአካል 97 ሺህ 372፤ በበይነ-መረብ 3 ሺህ 74 በድምሩ 100 ሺህ 446 ሰዎች ተሳትፎ አድርገዋል።

የተሳታፊዎች ብዛት ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔዎች ከፍተኛው መሆኑ ተገልጿል።

በጉባዔው ላይ ከአገራት በተጨማሪ የንግድ ተቋማት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተውበታል።

የዓለምን ሙቀት በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ ለመገደብ የሚያስችሉ ዓለም አቀፋዊ መፍትሔዎችን ማፈላለግ፣ አገራት  እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 2025 ብሔራዊ አየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ዕቅዳቸውን በመከለስ ተጨማሪ ግቦችን ማስቀመጥ፣ አረንጓዴ ሽግግርን ማፈጠንና የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ግቦችን ማሳካት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሲመክር ቆይቷል።

በኮፕ 28 ከዚህ ቀደም በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የተፈረሙ ስምምነቶችና ሌሎች ዕቅዶችን ተፈጻሚ ማድረግና ዕቅዶችን በፍጥነት ወደ ትግበራ ማስገባት እንደሚያስፈልግ በስፋት ተነስቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ የአየር  ንብረት ለውጥ  ተፅዕኖ ለመቋቋም ሀገር በቀል መፍትሔዎች ሥራ ላይ መዋላቸውን አመልክተዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፣ የምግብ ሥርዓቱን  ማሻሻል፣  አገር አቀፍ የስንዴ  ምርት ፕሮግራምና  የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብርን በስፋት ተግባራዊ ከተደረጉ መፍትሔዎች መካከል አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነት ተግባራዊ መደረጉን  በተጨባጭ የሚያሳዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉም ብለዋል።

በአየር  ንብረት ለውጥ  ተፅዕኖ የተጎዱ ሀገራት የዕዳ ጫናን ለመቀነስ፣ የአየር ንብረትን ለመቋቋም እና ፍትሃዊ እና ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ግባቸውን እንዲያሳኩ የቡድን 20 አባል ሀገራት ሰፊ እና ወቅታዊ  የዕዳ ማቃለያ ዕቅዶችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከጉባዔው ጎን ለጎን ከኩባ ፕሬዝዳንት ሚጉዌል ዲያዝ-ካኔል እና ከቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዲ ክሮን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በጉባዔው ላይ እየተሳተፉ ያሉ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮችም ከአቻዎቻቸው ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶች አካሂደዋል።


 

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ አውደ-ርዕይ (ፓቪሊዮን) የበርካታ አገራት፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ልዑካን ጎብኝተዋል።

ጎብኚዎቹ ከኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ተሞክሮ የሚሆኑ ሥራዎችን ለመመልከት እንደቻሉ ገልፀዋል።

የጉባዔው አዘጋጅ አገር የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ መሐመድ አል ናህያንና የእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ከጎብኚዎቹ  መካከል ይጠቀሳሉ።

በፓቪሊዮኑ የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የአካባቢ ጥበቃና ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች የተመለከቱ ውይይቶች ተካሂደዋል።

ናይጄሪያ የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከተ ውይይት በኢትዮጵያ ፓቪሊዮን አድርጋለች።

በምስራቅ አፍሪካ 300 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ግዙፉ የንፋስ ኃይል ማመንጫ በ600 ሚሊየን ዶላር በኢትዮጵያ መገንባት የሚያስችል ስምምነት በገንዘብ ሚኒስቴርና አሜአ ፓወር ከተሰኘ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ኩባንያ መካከል ተፈርሟል።

ኢትዮጵያና ጣልያን በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ በትብብር ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

ኢትዮጵያ በኮፕ 28 ያደረገችው ተሳትፎ ስኬታማ እንዲሁም  በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና አረንጓዴ ልማት እያከናወነች ያለውን ሥራ ለተቀረው ዓለም በሚገባ ያሳወቀችበት ዓለም አቀፍ መድረክ እንደሆነም ተገልጿል።

28ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 28) ዛሬ አመሻሹ ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም