ማርሽ ለዋጭ ቴክኖሎጂዎች ለስንዴ ምርትና ምርታማነት ማደግ 

በመንበረ ገበየሁ- ከሀዋሳ ኢዜአ

ባለፉት ሁለት ዓመታት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስራ ምርቱን ወደ ውጭ እስከመላክ የደረሰ አመርቂ ውጤት የተመዘገበበት ነው።

በመላው አለም ተፈላጊ የሆነው ስንዴ በቀላሉ ወደ ምግብነት የሚቀየር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የበርካታ ሃገራት ቀዳሚ ምርጫ መሆኑም ይነገራል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላቸው ሃገራትም የስንዴ ልማትን በትኩረት ያከናውናሉ።

እንደ ሀገር በመንግስት ልዩ ትኩረት የተሰጠው የስንዴ ልማት ስራ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ወደ ውጭ ተልኮ ምንዛሪን ማስገኘት የሚያስችል ግብ የተቀመጠለት ነው።

የስንዴ ልማት ስራው ከአርሶ አደር ማሳ እስከ ሰፋፊ የመንግስትና የግል መሬቶች ላይ የሚከናወንና መስኖን የበለጠ እንድንለማመድ ያስቻለ ነው።

ከተያዘው ግብ አንጻር ስራውን ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ሲቻል እንደሆነም ይታመናል።

በምርምር የተደገፉ ዝርያዎችን ማላመድ፣ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ማስተዋወቅና ሌሎች የኤክስቴንሽን ፓኬጆች እንዲተገበሩ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ተብለው የሚታሰቡት ደግሞ የግብርና ምርምር ማእከላት ናቸው።

በመላ ሃገሪቱ በሚገኙ 22 ማእከላቱ አማካኝነት በግብርናው መስክ ለሚከናወኑ ተግባራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ሚናውን የሚወጣው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በስንዴ ልማት ስራው አበርክቶውን እንዴት እየተወጣ ነው ስንል ጠይቀናል።

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኤክስቴንሽን ምርምር አስተባባሪ ዶክተር አዲሱ በዛብህ ስንዴ ለምግብ ዋስትና ከተለዩ 10 የምግብ ሰብሎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የስንዴን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር በምርምር ኢንስቲትዩቱ የልህቀት ማእከላት የሚወጡ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በሰፋፊ ማሳዎች በኩታ ገጠም በማልማት ለአርሶአደሩ የማስተዋወቅና የማላመድ ስራ እየተከናወነ ነው።

በዚህ ሂደትም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ አርሶአደሮች ስንዴን በስፋት አምርተው ከምግብ ዋስትና በዘለለ ለገበያ በማቅረብ ለሀገር ኢኮኖሚ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ምርምር ማእከሉ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

የስንዴን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከምርምር ማእከሉ የሚወጡ በሽታን የሚቋቋሙና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አዳዲስ ዝርያዎችን ከማስተዋወቅ ባለፈ አርሶአደሩ ቴክኖሎጂውን በአግባቡ እንዲጠቀም ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር ስንዴ ለምግብ ዋስትናና ለውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ አቅም መሆኑ ታውቆ በመንግስት የተጀመረው ስራ ውጤታማ እንዲሆን የግብርና ምርምር ማእከላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በምርምር ኢንስቲትዩቱ ስር በሚገኙ የምርምር ማእከላት ስራው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ሲሆን በዋናነትም ምርታማነትን የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅና የማላመድ ስራ ተጠቃሽ ነው።

የወንዶገነት ግብርና ምርምር ማእከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፊሊጶስ በበኩላቸው እንደ ሀገር  የስንዴ ምርምር ስራ ከ1960ዎቹ ጀምሮ መከናወኑን ገልጸው በዚህም ከ80 በላይ የስንዴ ዝርያዎችን ማስተዋወቅ እንደተቻለ ተናግረዋል።

ምርምር ማእከላት በዘርፉ የሚያደርጉት ምርምር የምርታማነት አቅምን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው ምርታማነቱ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል ብለዋል። ይሁን እንጂ ስንዴ አምራች የሆኑ ሌሎች ሃገራት በሄክታር ከሚያገኙት ምርት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ለዚህም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሚታየውን ክፍተት እንደ ችግር  አንስተዋል።

ምርምር ማእከሉ በሚሰራቸው የአርሶ አደር ሰርቶ ማሳያዎች በሚደረገው የባለሙያዎች ክትትል የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ፓኬጆችን በተገቢው የሚተገብሩ አርሶ አደሮች እንደ ሀገር በአማካይ በሄክታር ከሚገኘው ምርት በላይ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

መንግስት በስንዴ ልማት ላይ የጀመረው ስራ ከውጭ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገባውን ስንዴ እስከማስቀረት የደረሰ መሆኑን የገለጹት አቶ ሙሉቀን ለተያዘው ግብ ቀጣይነት ምርምር ማእከላት ከፍተኛ ሃላፊነት አለብን ብለዋል። 

በዚህም በሰፋፊ ማሳዎች የተጀመሩ የኩታ ገጠም የስንዴ ልማት ስራዎችን በማስፋት አርሶ አደሩ ተሞክሮ እንዲቀስም ማድረግና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙን እንዲያሳድግ መስራት ይገባል።

የኩታ ገጠም ልማት ስራው በድህረ ምርት ወቅት የሚያጋጥመውን 30 ከመቶ በላይ የምርት ብክነት በማስቀረት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።

እንደሃገር ከስንዴ ምርት በሄክታር በአማካይ የሚገኘው 32 ኩንታል መሆኑን የገለጹት አቶ ሙሉቀን አሁን በስፋት የተጀመረውን የስንዴ ልማት ስራ በቴክኖሎጂ ካስደገፍነውና በምርምር ካገዝነው በእጥፍ የማሳደግ አቅም መኖሩን ተናግረዋል።

ለዚህም ምርምር ማእከሉ ከተለያዩ ክልሎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጀት የጀመረውን ምርታማነትን የማሳደግ ስራ አጠናክሮ በማስቀጠል እንደሃገር ለተያዘው የስንዴ ልማት ስራ ውጤት ሃላፊነቱን ይወጣል።

ስንዴ እንደ ቡና ሁሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ሰብል እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ በሃገር አቀፍ ደረጃ ምርቱን የማስፋፋት ስራ ትኩረት እንደተሰጠው የሚናገሩት ደግሞ በምርምር ማእከሉ የግብርና ኤክስቴንሽን ተመራማሪ አቶ ዋሲሁን አለምነው ናቸው።

እንደተመራማሪው ገለጻ የስንዴ ልማቱ በምርምር የተለዩ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ከመጠቀም ጀምሮ ሙሉ ፓኬጁን በማሳ ላይ በመተግበር ከተሰራ ምርታማነትን በማሳደግ እንደሃገር የተያዘውን ግብ በዛላቂነት ማሳካት ይቻላል።

ለዚህም ምርምር ማእከሉ በሰፋፊ ማሳዎች ላይ በኩታ ገጠም ማልማት የጀመራቸው ስራዎች ማሳያ መሆናቸውን ገልጸው ስንዴ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ሰብል መሆኑ አጠያያቂ አይደለም ብለዋል።

ከዘር አመራረጥ እስከ ድህረ ምርት አሰባሰብ ድረስ ያለውን ፓኬጅ በአርሶአደር ማሳ ላይ በመተግበር ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶአደሩንና የግብርና ባለሙያዎችን በስልጠና እስከማብቃት የደረሰ እገዛ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም በየአካባቢው ትርፍ አምራች አርሶአደሮችን በመፍጠር መንግስት በሰፋፊ መሬቶች ላይ የሚያለማውን የበጋ መስኖ ስንዴ ስራ ለማገዝ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

ማእከሉ መዓዛማና መድሃኒት እጽዋቶችን ከማላመድና ማስተዋወቅ ተልእኮው በተጨማሪ ስንዴ ላይ በሲዳማ፣ በኦሮሚያና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሲዳማ ክልል ሁላ ወረዳ 28 አርሶ አደሮችን አሳትፎ በ20 ሄክታር ላይ በኩታገጠም ያለማው የስንዴ ልማት ስራ ሙሉ ፓኬጁን በመተግበር የተከናወነና ለሌሎች ወረዳዎች ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ስራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የአርሶአደሮች ቀን መርሃግብርን በማዘጋጀት በሰፋፊ ማሳ ላይ የተከናወኑ የስንዴ ልማት ስራዎችን ማስጎብኘት በዘርፉ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል የእርሻ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ባንጉ በቀለ በክልሉ በመኸር ወቅት ከ12ሺ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ስንዴ በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች የሁላ ወረዳ ቀዳሚው መሆኑን ጠቅሰው የወንዶ ገነት ምርምር ማእከል በምርምር የተደገፉ ዝርያዎችን በስፋት ማስተዋወቁ በአካባቢው ያለውን አቅም በተገቢው ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል።

አርሶ አደሮችን በክላስተር በማቀናጀት የተከናወነው የስንዴ ልማት ስራም ውጤታማና እንደተሞክሮ ሊወሰድ የሚችል በመሆኑ ቢሮው በሌሎች ወረዳዎችም እንደሚያሰፋው ጠቅሰዋል።

ለስራው ውጤታማነት የምርምር ማእከሉ ከመንግስትና አርሶአደሮች ጋር ተቀናጅቶ መስራቱ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል ያሉት ሃላፊው ዝርያን ከማስተዋወቁ ባሻገር የስንዴ ማሳው በክላስተር መልማቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ያስገኛል ብለዋል። 

በወረዳው የሉዳ ቀበሌ ግብርና ባለሙያ አቶ ሽፈራው ሸኖ አካባቢው ስንዴ በስፋት የሚመረትበት ቢሆንም በኩታገጠም የማምረት ልምድ አለመኖሩን ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወንዶገነት ግብርና ምርምር ማእከል በሰፋፊ የአርሶአደር ማሳ ላይ በጀመረው ስራ የአርሶአደሩን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በዚህም የአርሶ አደሩን ክህሎት በማሳደግ በቀበሌው ከ80 ሄክታር በላይ ስንዴ በኩታ ገጠም እየለማ ነው ብለዋል።

ምርምር ማእከሉ 28 አርሶአደሮችን በማሳተፍ በ20 ሄክታር ማሳ ላይ የሰርቶ ማሳያ ልማት ማከናወኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ ተሞክሮ እንዲወስዱ ያስቻለ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።


 

በቀበሌው የሞሮቾ መንደር ነዋሪ አርሶአደር ዱባለ ገመዳ ባለፉት ሁለት ዓመታት ስንዴን በክላስተር ማምረት በመጀመራቸው  ምርታማነታቸው መጨመሩን ተናግረዋል።

ምርምር ማእከሉና ወረዳው በሚሰጣቸው ድጋፍ ከስንዴ ምርታቸው ተገቢውን ምርት ለማግኘት ሙሉ ፓኬጁን በአግባቡ እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸው የኩታ ገጠም ልማት ጥሩ ተሞክሮ የምንለዋወጥበት ነው ብለዋል።

የስንዴን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አገሪቷ ከውጭ የምታስገባውን በማስቀረት የውጭ ምንዛሬን ማምጣት እንደሚቻል የታየው ተሞክሮ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከግብርና ሚኒስቴር እስከ አርሶ አደሩ ያሉ አካላት ትኩረታቸውን ከስንዴ ልማት ባለማንሳት ለቀጣዩ ትውልድ የብልጽግና ተምሳሌት የሆነችን አገር ለማውረስ ልንሰራ ይገባል እላለሁ ። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም