ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ የሚያቀርበውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ የሚያቀርበውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2016(ኢዜአ)፦ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ የሚያቀርበውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የ2024 የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታን በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ቀንድ በተደጋጋሚ በርካታ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት ነው።
ይህም ደግሞ በተለይም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የመጣ መሆኑን ገልጸው እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የተቀናጀ ሥልታዊ ትብብር ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ለማቃለል የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ገቢራዊ በማድረግ የራሷን አስተዋጽዖ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ለራሷ ከምታደርገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ከጎረቤት አገራት ጋር በመቀናጀትም የጋራ ጠንካራ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራች መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2023 ለሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋል ብላ በእቅድ ከያዘችው 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር 30 በመቶ ብቻ እንዳገኘች ገልጸዋል።
ይህም ከእቅዱ አንጻር ሲታይ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍም በአብዛኛው ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚውል መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም የአደጋ ተጋላጭነት ቅነሣ ሥራ ላይ የሚውለው የፋይናንሰ ኃብት ጥቂት መሆኑን ገልጸው ይህም ሚዛናዊ የሃብት ክፍፍል በማድረግ ሊስተካከል ይገባል ነው ያሉት።
ከዚህ አንጻር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሰብዓዊ እርዳታ ዘርፍ ዘላቂና ተገማች የፋይናንስ ፈሰስ ማድረግ እንዳለበት ነው ያመላከቱት።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ተወካይ ራሜሽ ራጃሲንግሃም በበኩላቸው በፈረንጆቹ 2024 በአፍሪካ 140 ሚሊየን ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።
ለዚህም የአየር ንብረት ለውጥና የወረርሽኞች መከሰት እንዲሁም በዜጎች መካከል ያለው የገቢ እኩልነት መዛባት ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ነው ያስረዱት።
በተለይም ሴቶችና ሕጻናት ተጎጂነታቸው ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸው እነዚህን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች በስፋት መከናወን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።