የልዩ ኢኮኖሚ ዞን የአምራች ዘርፉን አቅም ለማሳደግ እድል የሚፈጥር ነው - የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የልዩ ኢኮኖሚ ዞን የአምራች ዘርፉን አቅም ለማሳደግ እድል የሚፈጥር ነው - የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2016 (ኢዜአ)፦ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን የአምራች ዘርፉን አቅም ለመጨመር ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ አዋጅ ላይ ያዘጋጀው ይፋዊ የሕዝብ ውይይት ዛሬ ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የምክር ቤቱ የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት እንዲሁም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
መንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሥርዓት የሚቀይር ፖሊሲ ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን ከፖሊሲው የመነጨ የልዩ የኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ፤ ረቂቅ አዋጁ በርካታ ተቋማቶችና ባለኃብቶች በዘርፉ ልማት በአምራች ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፉና ከዚህ ቀደም ለአልሚዎች ክፍት ያልነበሩ ሥራዎች ክፍት የሚሆንበትን እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
ከዚህ ቀደም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የነበረውን የአምራችነት አቅም ችግር ለመፍታትና ምርታማነትን ለመጨመር ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ መልካም እድል ይዞ እንደሚመጣ ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የነበሩ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን እንደ መልካም ተሞክሮ በመውሰድ በኢኮኖሚ ዞኖቹ በተሻለ መልኩ አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አልሚ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቀው ዝቅተኛ የካፒታል መጠን 75 ሚሊየን ዶላር ወይም አምስት ቢሊየን ብር እንደሚሆንና በአንድ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አልሚ ጠያቂነት ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተብሎ የሚሰየም ይዞታ 75 ሄክታር እንደሆነ ረቂቁ ያመለክታል።
በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለኃብቶችም ፈቃድ ለማግኘት 200 ሺህ ዶላር ተቀማጭ ማድረግን የሚጠይቅ መሆኑንም ነው ምክትል ኮሚሽነሩ ያነሱት።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል መኮንን የረቂቅ አዋጁ መዘጋጀት ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ ዞን አልሚ ፈቃድ ለማግኘት የተቀመጠው የካፒታል መጠንና የመሬት አቅርቦት አለመመጣጠን እንደሚታይበት ጠቅሰው የአገሪቷን የመሬት ሃብትና የካፒታል ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ማስተካከያ መደረግ አለበት ብለዋል።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የኮሙኒኬሽንና የፕሮሞሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ማሞ በበኩላቸው በረቂቅ አዋጁ ለውጭ ባለሀብቶች የፈቃድ አሰጣጥ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና አሰራሮችን ያማከለ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አማረች ባካሎ በበኩላቸው የረቂቅ አዋጁ መዘጋጀት በአምራች ዘርፉ ተወስኖ የነበረውን አሰራር በማስፋት ስብጥር ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ አዋጁ ዳብሮ እንዲጸድቅ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።