ቀጥታ፡

የፈጠራ ተሰጥዖ ያላቸው ወጣቶችን መደገፍና ማብቃት ይገባል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2016 (ኢዜአ)፦ የፈጠራ ተሰጥዖ ያላቸው ወጣቶችን በመደገፍና ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ተግባር በመለወጥ አገራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በሳይንስ ሙዚየም ከዛሬ ጀምሮ ለስድስት ቀናት የሚቆየውን የአቪዬሽን ኢኖቬሽን 2016 ኤክስፖ በይፋ ከፍተዋል። 

በኤክስፖው የአገራችን ቀጣይ ስኬትና ተስፋ የሚያመላክት የፈጠራ ሥራዎች እንደቀረቡ ገልፀዋል።


 

የዘመኑን ፈጠራ ውጤቶች በመጠቀም በመፍጠርና በመፍጠን ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ እንዲሁም አሰራር በማዘመን የተሻለች አገር ለአዲስ ትውልድ ማስረከብ አለብን ነው ያሉት።

በተለይም ትውልዱ ለዕውቀትና ለሥራ የሚተጋና ዘመኑን የሚጠቅም አስተሳሰብ እንዲይዝ መሥራት ይገባል ብለዋል።   

ንድፈ ኃሳብ ያለ ተግባር ዋጋ የለውም ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር በመተርጎም አገራዊ ብልፅግና ማረጋገጥ አለብን ብለዋል። 

ወጣቶች በዘርፉ ወደ ምርምር እንዲገቡና የማኅበረሰብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የፈጠራ ሥራዎችን ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።  

ለዚህም የፈጠራ ተሰጥዖ ያላቸው ወጣቶችን በመደገፍ ረገድ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል። 

መንግሥትም ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ጠቅሰው፤ መሰል አውደ ርዕዮችም ሊጠናከሩ ይገባል ነው ያሉት። 


 

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ  በበኩላቸው የአቪዬሽን ዘርፉ በኢትዮጵያ አንጋፋ ቢሆንም በውጭ አገራት ምርቶች ጥገኛ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በአቪዬሽን ኢኖቬሽን ረገድ ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ በመሆኑ በተለይም ወጣቶች በማበረታታት ተስፋ ሰጭ የፈጠራ ውጤቶች እየመጡ ነው ብለዋል።

በሁሉም የሙያ መስክ የፈጠራ ሥራዎች እየተበረታቱ በመምጣቱ ተጨባጭ ውጤቶች መምጣታቸውን ገልፀው፣ በአቪዬሽን ዘርፍ በአገር በቀል ዕውቀት እየታገዙ መደገፍ ያስፈልገናል።

ኤክስፖው ፋይዳው ለዘርፉ ትኩረት አቅጣጫዎች የሚያመለክት እንደሆነም ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግሥቴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን የልህቀት ማዕከል በማድረግ በዓለም ተወዳዳሪ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ለመገንባት ራዕይ ተነድፎ እየሰተራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኤክስፖ ዓላማ በአቪዬሽን መስክ በፈጠራ ሥራ ላይ የተሰማሩና የወደፊቱን የአቪዬሽን ምህዳር በመቀየር ረገድ በፈጠራ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማበረታታት ነው ብለዋል።

ለስድስት ቀናቱ ኤክስፖ 95 ወጣቶች በጋራና በተናጠል ሆነው 90 የፈጠራ ውጤቶቻቸውን እንዲሁም 34 የግልና መንግሥታዊ ተቋማትም በአቪዬሽን ዘርፍ ምርትና አገልግሎታቸውን ለዕይታ አቅርበዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎች ውድድር የሚኖር ሲሆን የተሻለ የፈጠራ ውጤቶችን ላቀረቡና ከ15 ለማያንሱ ወጣቶች ዘላቂ ድጋፍ የሚያገኙበትም ሁኔታ ተመቻችቷል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም