የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የሚከናወኑ የእርምት እርምጃዎች የሚበረታቱ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ የሚከናወኑ የእርምት እርምጃዎች የሚበረታቱ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2016 (ኢዜአ)፦የመንግሥት ተቋማት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈፅሙ የሚሰጡ ምክረ ኃሳቦችን ተከትሎ የሚወሰዱት የእርምት እርምጃዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ የጸደቀበት 75ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የሰብዓዊ መብት ቀን ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ መሰረታዊ ከሆኑ የሰብዓዊ መብት ዓለም አቀፍ ሰነዶች አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ ሰነዱ ከ75 ዓመታት በፊት በጸደቀበት ወቅት ከፈረሙ 3 የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ እንደነበረች አስታውሰው መንግሥት የሰብዓዊ መብትን ለማስከበር በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት አበረታች እርምጃዎችን መውሰዱን አብራርተዋል።
የፖለቲካ ምህዳሩን ክፍት በማድረግ፣ ለሰብዓዊ መብቶች ተቋም የተሰጠው ትኩረት በተለይም የሰብዓዊ መብቶች ተቋም ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም የተሰጠውን ድጋፍ ከተወሰዱ እርምጃዎች ውስጥ ዘርዝረዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሚያከናውናቸው የምርመራ ሥራዎች የሚሰጣቸውን ምክረ ኃሳቦችን ተግባራዊ በማድረግና እርምጃ በመውሰድ የተጀመሩ ተግባራትም የሚበረታቱ ናቸው።
በኢትዮጵያ የተጀመሩ የሽግግር ፍትሕና አገራዊ ምክክር ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚያግዙ ገልጸው ኮሚሽኑ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ምክረ ኃሳቦችን በማቅረብ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ በማካተት እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
የተባበሩት መንሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ የጸደቀበት 75ኛ ዓመት በሚከበርበት ወቅትም የበለጠ ለመሥራት ቃላችንን የምናድስበት ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ማርሴል አክፖቮ ኢትዮጵያ ለተቋማት ግንባታ፣ ፖሊሲና ለሰብዓዊ መብት የሰጠችው ትኩረት የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በበኩላቸው ኅብረቱ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሰላም ሥምምነቱን በመተግበር፣ የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ በማድረግና በአገራዊ ምክክር እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብትን ለማረገገጥ ለምታከናውነው ተግባር ኅብረቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።