የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የሀገራት የስትራቴጂክ አጋርነት መገንቢያ ማዕከል ነው - የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የሀገራት የስትራቴጂክ አጋርነት መገንቢያ ማዕከል ነው - የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2016 (ኢዜአ)፦ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ/አፍሌክስን የአህጉሪቱን ብልጽግና ለማሳካት የሚሰራ የተሟላ ተቋም እንዲሆን የማገዝ ፍላጎት ማሳየታቸውን አቶ ዛዲግ አብርሃ ገለጹ፡፡
የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የአካዳሚውን የሽግግር ስትራቴጂ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አካዳሚው እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2021 እንደገና ተደራጅቶ ሪፎርም ካደረገ በኋላ ተቋማዊ አቅሙን በማስፋት እምርታዊ ለውጥ ለማስመዘገብ 13 ፕሮጀክቶችን መንደፉ ተገልጿል፡፡
አካዳሚው በትብብር ላይ ከተመሰረተው መርሁ በመነሳት ከሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብርና በቅንጅት የሚሰራባቸው ስምንት መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀቱም ተጠቅሷል፡፡
ከእነዚህም መካከል የአመራር ልማት ፕሮግራም፣ አፍሪካዊ ተቋም አድርጎ መገንባት፣ ሱሉልታን እንደ ዳቮስ፣ አዳዲስ እሳቤዎችን ማመንጨት፣ የአመራሮችና ተቋማት እውቅናና ሽልማት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
አቶ ዛዲግ አብርሃ እንዳሉት፤ አካዳሚው ለስራዎቹ መሳካት የሚያግዙ ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አመራሮች እውቅና የሚሰጥ አፍሪካዊ ተቋም ይሆናል ነው ያሉት፡፡
አካዳሚውን ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካውያን የሚሳተፉበትና የአህጉሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚሰራ ተቋም እንዲሆን ፕሮጀክት መነደፉን ገልጸው፤ ለዚህም ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ቀንበር እንዲወጡና አፍሪካዊ ተቋማት እንዲመሰረቱ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቷን አስታውሰው፤ ዛሬም ዘመኑን የዋጀ አመራር ለማፍራት ጥረት እያደረገች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
አካዳሚው የኪነ ህንጻና የግቢው ቅርጽ አፍሪካን እንዲወክል ተደርጎ፤ ህንጻዎቹ በአፍሪካ መሪዎች እንደሚሰየሙ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞቹ አፍሪካን ያካተቱ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የሀገራት የስትራቴጂክ አጋርነት መገንቢያ ማዕከል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ ጋር ትብብር ለሚሹ ሀገራትና ተቋማት መግቢያ በር መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ሀገራትና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በተደረገ ውይይት አካዳሚውን የማገዝና ግዙፍ ተቋም የማድረግ ፍላጎት እንዳለ ተገንዝበናል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭገኒ ተረክሂን የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም እያስመዘገበ ያለው ውጤት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀደምት አመራሮች በሶቪዬት ህብረት የአመራር አካዳሚ ስልጠና ይወስዱ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህ የመተባበር ባህል ዛሬም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
አክለውም አካዳሚውን ከሩሲያ አካዳሚና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በማስተሳሰር የተቋቋመለትን ግብ እንዲመታ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡