ቀጥታ፡

በአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ የኢትዮጵያን መፃዒ ተስፋ የሚጠቁሙ አበረታች የፈጠራ ተግባራት ቀርበውበታል- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2016(ኢዜአ)፦ በአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ የኢትዮጵያን መፃዒ ተስፋ የሚጠቁሙ አበረታች የፈጠራ ተግባራት መቅረባቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ  በሳይንስ ሙዚየም ከዛሬ ጀምሮ ለስድስት ቀናት የሚቆየውን የአቪዬሽን ኢኖቬሽን 2016 ኤክስፖ በይፋ ከፍተዋል። 

በኤክስፖው የሀገራችንን ቀጣይ ስኬትና ተስፋ የሚያመላክት የፈጠራ ስራዎች እንደቀረቡ ገልፀዋል።

የዘመኑን ፈጠራ ውጤቶች በመጠቀም በመፍጠርና በመፍጠን ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ እንዲሁም አሰራር በማዘመን የተሻለች ሀገር ለአዲስ ትውልድ ማስረከብ አለብን ነው ያሉት።

በተለይም ትውልዱ ለዕውቀትና ለስራ የሚተጋ፣ ዘመኑን የሚጠቅም አስተሳሰብ እንዲይዝ መስራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

ንድፈ ሀሳብ ያለ ተግባር ዋጋ የለውም ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር በመተርጎም ሀገራዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል። 

በኤክስፖ የቀረቡ ሀሳቦች የሀገር ችግርን መሰረት ያደረጉ እና ትልቅ ተስፋ የሚሰጡ እንደሆኑ ነው ያነሱት።

የስራ ፈጠራን ማበረታታትና አዳዲስ ዕውቀቶችን በመተካት ነባርና ጎታች አሰራርን በማዘመን ያደገችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ አለብን ነው ያሉት። 

የፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶችን በመደገፍ ረገድ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተለይ ወጣቶች በዘርፉ ወደ ምርምር እንዲገቡና ነገን አሻግረው የሚያዩ፣ በምግባር የታነፁ እንዲሆኑ ማስቻል፣ የማህበረሰብ ተጠቃሚነት የሚያመጡ ፈጠራ ስራዎችን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ 

መንግስትም ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ጠቅሰው፤ መሰል አውደ ርዕዮችም ሊጠናከሩ ይገባል ነው ያሉት። 

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒሰትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ በበኩላቸው የአቪዬሽን ዘርፉ በኢትዮጵያ አንጋፋ ቢሆንም በውጭ አገራት ምርቶች ጥገኛ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በአቪዬሽን ኢኖቬሽን ረገድ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ በመሆኑ በተለይም ወጣቶች በማበረታታት ተስፋ ሰጭ የፈጠራ ውጤቶች እየመጡ ነው ብለዋል።

በሁሉም የሙያ መስክ የፈጠራ ስራዎች እየተበረታቱ በመምጣታቸው ተጨባጭ ውጤቶች መምጣታቸውን ገልፀው፣ በአቪዬሽን ዘርፍ በሀገር በቀል ዕውቀት እየታገዙ መደገፍ ያስፈልገናል።

ኤክስፖው ፋይዳው ለዘርፉ ትኩረት አቅጣጫዎች የሚያመለክት እንደሆነም ገልፀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም