ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ  እየተስራ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ  መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ገለጸ።

"ፈጠራ ለአቪዬሽን ልህቀት" በሚል መሪ ሃሳብ" የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ 2016  በሳይንስ ሙዚየም በይፋ ተከፍቷል።

በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ፤ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ቴክኖሎጂና ካፒታል የሚጠይቅ፣ በዓለም ዓቀፍ ስታንዳርዶችና ሕጎች የሚመራ፣ ጠንካራ ውድድር የሚታይበት፣ ተለዋዋጭና ውስብስብ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን የልህቀት ማእከል በማድረግ በዓለም ተወዳዳሪ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ለመገንባት ራዕይ ተነድፎ እየሰተራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በተጨማሪም የአቪዬሽን ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም አቅም በማሳደግ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግና በቀጣይም የአቪዬሽን ቴክኖሎዎች ባለቤት ማሳደግ  ላይ በትኩረት  እንደሚሰራ  ጠቅሰዋል።

የአቪዬሽን ኢኖቬሽን ኤክስፖ ዓላማም በአቪዬሽን መስክ በፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩና የወደፊቱን የአቪዬሽን ምህዳር በመቀየር ረገድ በፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች የበኩላቸውን አወንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ለስድስት ቀናት በሚቆየው ኤክስፖ 95 ወጣቶች በጋራና በተናጠል ሆነው 90 የፈጠራ ውጤቶቻቸውን እንዲሁም 34 የግልና መንግስታዊ ተቋማትም በአቪዬሽን ዘርፍ እያከናወኑ ያሉትን ስራዎቻቸውንና የፈጠራ ውጤቶቻቸውን አቅርበዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎች ውድድር የሚኖር ሲሆን የተሻለ የፈጠራ ውጤቶችን ላቀረቡና ከ15 ለማያንሱ ወጣቶች ዘላቂ ድጋፍ የሚያገኙበትም ሁኔታ ተመቻችቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም