ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2016 (ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዡ ቢንግ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ለጀመረቻቸው ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ቻይና በባለ-ብዙ ወገን ጉባኤዎች ላይ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ ጠቅሰው በተለይ ኢትዮጵያ የብሪክስ ሀገራትን እንድትቀላቀል ላድረገችው ድጋፍ አድንቀዋል።
በተጨማሪም ቻይና በኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው እድገት እውን እንዲሆን በተለያዩ ዘርፎች የምታደርገውን ድጋፍና በአፍሪካ የጸጥታ፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ያላትን ሚና አድንቀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያውን ሙሉ ስምምነት ለመተግበር በመንግስት በኩል ያለውን ቁርጠኝነትም አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ ቀንድ የቻይና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዡ ቢንግ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ ያሳየውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ያላትን ሚና ያነሱት አምባሳደር ዡ የሰላም ሂደቱ ትግበራ አበረታች መሆኑንም አክለዋል።
አምባሳደሩ ሁለተኛውን የቻይና-የአፍሪካ ቀንድ የሰላም፣የመልካም አስተዳደርና የልማት ጉባኤ መካሄድ አስፈላጊነት ላይም አጽንኦት መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።