ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ናቸው- የጃፓን ባለሀብቶች

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 1/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መሆናቸውን የጃፓን ባለሀብቶች ገልጸዋል።

በኢትዮ-ጃፓን የኢንቨስትመንት ፎረም የተሳተፉ የጃፓን ባለሀብቶች እና የስራ ኃላፊዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሚተዳደሩትን የቦሌ ለሚ እና ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጎብኝተዋል። 

ልዑካን ቡድኑ በጉብኝታቸውም የፓርኮቹን መሰረተ ልማት ፤ ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ እንዲሁም የሌሎች ባለሀብቶችን ተሳትፎ ተመልክተዋል።

በወቅቱም በፓርኮቹ ኢንቨስት ቢያደርጉ የሚያገኟቸውን የኢንቨስትመንት አስቻይ ሁኔታዎችና ማበረታቻዎች  ገለፃ ተደርጎላቸዋል።

 በኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘመን ጁነዲን በኢትዮጵያ እና በጃፓን መካከል የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ቢኖርም በኮርፖሬሽኑ ስር በሚተዳደሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የጃፓን ባለሀብቶች ያላቸው ተሳትፎ እንደ ግንኙነቱ ግዝፈት አለመሆኑን ጠቅሰዋል።  


 

ኮርፖሬሽኑ ይህንን ለመቀየርም በዘርፉ ጠንክሮ በመስራት ባለሀብቶቹን ለማስተናገድ ከምጊዜውም በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል። 

አቶ ዘመን አክለውም የጃፓን ባለሀብቶች  በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ቅድመ ዝግጅት መሰራቱንና በቀጣይም ተሳትፎአቸውን  ለማሳደግ  ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በጃፓን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር እንደሚሰራ  ገልፀዋል። 

የልዑካን ቡድኑን የመሩት የኢንስፓየር አፍሪካ አሶሴሽን ዳይሬክተር ያማጉቺ  ፓርኮቹ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች የተሟላ መሰረተ ልማትና ምቹ የስራ አከባቢ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

ባለሀብቶቹም ገብተው መዋለ ኑዋያቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ አጠናክረው እንደሚሰሩ መግለጻቸውን  ከኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን  ማህበራዊ ድህረ ገጽ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም