የትግራይ ልማት ማህበር በክልሉ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን በማፍራት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን እያገዘ ነው--አቶ ጌታቸው ረዳ - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ልማት ማህበር በክልሉ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን በማፍራት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን እያገዘ ነው--አቶ ጌታቸው ረዳ
መቀሌ ፤ ህዳር 30/2016 (ኢዜአ)፡- የትግራይ ልማት ማህበር በክልሉ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን በማፍራት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን እያገዘ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ።
ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው ይህን የገለጹት በትግራይ ልማት ማህበር የተገነባውና 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሚያከብረው የቃላሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተዘጋጀ ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
በዚሁ መልዕክታቸው ልማት ማህበሩ ያስገነባው የቃላሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በክልሉ ውስጥ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።
ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በዚሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በርካታ አቅምና ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች መገኘታቸውን ጠቁመው፤ "የልማት ማህበሩ በአገራችን በተለያዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስራዎች በመሰማራት መሰረታዊ እድገት እንዲመዘገብ ድርሻው የላቀ ነው" ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት፤ ልማት ማህበሩ ዲጂታል ትምህርትን በማስፋፋት የመማርና ማስተማር ሂደት የዘመነ ለማድረግም የያዘው ራዕይ እውን እንዲሆን የክልሉ ህዝብ ከጎኑ በመሰለፍ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል።
የልማት ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር የማነ ታደሰ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአሥራ ሁለት ከተሞች ቃላሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት ተጀምሮ ግንባታቸው የተቋረጡትን ዳግም ግንባታቸውን ለማስጀመር አስፈላጊውን ዝግጅት ተጠናቋል።
ይህም በውጭ እና በአገር ውስጥ በሚገኙ የልማት ማህበሩ ደጋፊዎች እውን እንደሚሆን እምነታቸው ገልጸዋል።
በቃላሚኖ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተምረው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው የላቀ ውጤት ያመጡና በሥራ ዓለም የሚገኙ ከ2 ሺህ በላይ ከፍተኛ ባለሙያዎች መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ የልማት ማህበሩ ዳይሬክተር አቶ ተስፋይ ገብረእግዚአብሄር ናቸው።
ባለፈው ዓመት በስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና 700 ተማሪዎች ከ97 ነጥብ በላይ ማምጣታቸውን ዳይሬክተሩ አስታውሰው፤ ተማሪዎቹ በተያዘው የትምህርት ዘመን በዚሁ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መደበኛ ትምህርታቸው እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።