ቀጥታ፡

የሰላምና የአብሮነት የጋራ እሴቶችን አጎልብቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ምሁራን የድርሻቸውን አበርክቶ ሊያደርጉ ይገባል

ጂንካ፤ ህዳር 30/2016(ኢዜአ)፡- የህዝቦች የሰላምና የአብሮነት መገለጫ የሆኑ የጋራ እሴቶችን አጎልብቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ምሁራን የድርሻቸውን አበርክቶ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተመለከተ።

የአሪ ብሄረሰብ  የዘመን መለወጫ የድሽታ ግና በዓል ዋዜማ በጂንካ ከተማ በፓናል ውይይት እየተከበረ ነው።

የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የአብሮነትና የዕርቀ ሰላም ተምሳሌት የሆነው የድሽታ ግና በአል በየአመቱ  ታህሳስ አንድ በድምቀት ይከበራል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የአሪ ብሄረሰብ  የራሱ የዘመን አቆጣጠር ያለው ሲሆን በብሔረሰቡ አጠራር ''ሎንጋ'' ወይም ታህሳስ ወር አሮጌውን አመት ሸኝተው አዲሱን አመት ይቀበላሉ።


 

በመረሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ “ድሽታ ግና በአል የአሪ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያን ነው” ብለዋል።

ድሽታ ግና ለሰላም እሴት ግንባታ፣ለህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት መጠናከር እና ለሀገራዊ ልማትና ብልፅግና ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ክብረ በአል መሆኑንም አንስተዋል።

በድሽታ ግና በአል የመረዳዳት፣የአብሮነት እና ተካፍሎ የመብላት እሴት ጎልቶ የሚታይበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ድሽታ ግና ከሀገራችን አልፎ ለአለም ህዝብ የሚያበረከተው ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ክብረ በአል በመሆኑ እሴቱ ይበልጥ አድጎና ጎልብቶ ለትውልድ እንዲሻገር ብሎም በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ምሁራን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ባውዲ በበኩላቸው “የአሪ ማህበረሰብ ተዝቆ የማያልቅ በርካታ እሴት ያለው ህዝብ ነው” ብለዋል።

“የመረዳዳት፣የአብሮነት፣የዕረቀ ሰላም መሰረት የሆነው የድሽታ ግና በዓል የአሪ ማህበረሰብ እሴት መገለጫ  መሆኑን ጠቁመው እሴቱ ለዘመናዊ አስተዳደር፣ለዘላቂ ሰላምና ለአገረ መንግስት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አመልተዋል።

ሕብረ ብሔራዊነት የተጋመደባቸው የጋራ እሴቶችን በማጎልበት  ለአገር ሰላም፣ለልማትና ለአገር ግንባታ ለማዋል ምሁራን የራሳቸውን አበርክቶ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

በተለይ የብሔረሰቡ እሴት መገለጫ የሆነው የመረዳዳት ባህል ለሌሎችም ተምሳሌት የሚሆን መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሪ ዞን ማዕከል በጂንካ ከተማ እየተከበረ ባለው የበዓሉ ዋዜማ  ከፌዴራል ፣ከክልል እና ከዞን የተጋበዙ የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።

በዋዜማ ክብረ በአሉ የባህል መሪዎች፣የሀይማኖት አባቶች፣የአገር ሽማግሌዎችና የባህል ተመራማሪዎችም ተሳትፈዋል።

ዘንድሮ ለ8ኛ ጊዜ በአደባባይ እየተከበረ ያለው የድሽታ ግና በአል ነገ ታህሳስ 1/2016 ዓ.ም ''ለሀገራዊ ችግሮች ሀገራዊ መፍትሄ በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በድምቀት ይከበራል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም