የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 528 ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ሕብረተሰቡ ሊቀላቀሉ ነው

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 30/2016 (ኢዜአ)፡- የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 528 ታጣቂዎች በቅርቡ የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ሕብረተሰቡ ሊቀላቀሉ መሆኑን የሰሜን ምዕራብ ኮማንድ ፖስት የጎንደር ቀጣና ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል ዋኘው አለሜ ገለጹ፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠዳ ወረዳ የተሃድሶ ሥልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙት ታጣቂዎች መንግሥት ላደረገላቸው የሰላም ጥሪ አመስግነው ሕዝባቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባላት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው የተሃድሶ ሥልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙትን በመጎብኘት ከኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡


 

የሰሜን ምዕራብ ኮማንድ ፖስት የጎንደር ቀጣና ሰብሳቢ ብርጋዴር ጄኔራል ዋኘው አለሜ፤ በተለያዩ ቅስቀሳዎች በመደናገር ወደ ጫካ የገቡ ታጣቂዎችን ኮማንድ ፖስቱ መስፈርቶችን በማውጣት በወዶገብነት እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም በአማራ ክልል ጎንደር ቀጣና የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 528 ታጣቂዎች በቅርቡ የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ሕብረተሰቡ የሚቀላቀሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በጎንደር ቀጣና እስካሁን 528 ታጣቂዎች ጥሪውን መቀበላቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህ መካከልም 234 የሚሆኑት ከእነመሳሪያቸው የገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሚኖሩባቸው ቀበሌ እና ወረዳዎች የወንጀል ሪከርድ እንደሌላቸው ተረጋግጦና የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው አካባቢያቸውን የሰላም ዘብ በመሆን እንዲጠብቁ ይደረጋል ብለዋል።

ከ528ቱ ታጣቂዎች መካከልም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 119 የሚሆኑት የተሃድሶ ሥልጠና መውሰድ መጀመራቸውን ጠቁመው፤ ቀሪዎቹም በቅርቡ ሥልጠና እንዲጀምሩ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠዳ ወረዳ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የተሃድሶ ሥልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙት ታጣቂዎችም መንግሥት ላደረገላቸው የሰላም ጥሪ አመስግነው ሕዝባቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

እየተሰጣቸው ያለውን ሥልጠና በአግባቡ ተከታትለው በማጠናቀቅ በአካባቢያቸው የሰላም አምባሳደር እንደሚሆኑ ገልፀዋል።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባል ዶክተር አብርሃም በርታ፤ ታጣቂዎቹ የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በመሰልጠን ሕብረተሰቡን ለመቀላቀል መዘጋጀታቸውን በውይይቱ አረጋግጠናል ብለዋል።

ከተመላሽ ታጣቂዎቹ ጋር በነበራቸው ውይይትም ሥልጠናው የነበሩ ስህተቶችን ተገንዝበው ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱና ሕብረተሰቡን ለማገልገል ያዘጋጃቸው መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።ሌላኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አባል ሳዲቅ አደም፤ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በሥልጠና ላይ ያሉት ታጣቂዎች በሰላም ጉዳይ ላይ በቅንነት ለመሥራትና ሕብረተሰቡን ለማገልገል እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ በጎንደር ከተማ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም