በቴነሲ አውሎ ነፋስ ባስከተለው ጉዳት የስድስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

335

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 30/2016 (ኢዜአ)፡- በአሜሪካዋ ቴነሲ ግዛት ውሽንፍር የቀላቀለ አውሎ ነፋስ ባስከተለው ጉዳት በትንሹ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ።

በግዛቷ ከትላንት በስትያ ጀምሮ የተከሰተው ውሽንፍር የቀላቀለ አወሎ ነፋስ መጠነ ሰፊ ጉዳት ማድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል።

አውሎ ነፋሱ መኖሪያ ቤቶችን፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትንና ሌሎች ንብረቶችን ሲያወድም  የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉና 23 ሰዎች መጎዳታቸው ተገልጿል።

ከሟቾቹ መካከል ህጻናትና አዛውንት እንደሚገኙበት ያመለከተው ዘገባው ገሚሶቹ የግዛቷ ዋና ከተማ ናሽቪል ነዋሪ መሆናቸውን አስነብቧል።

የከተማዋ ከንቲባ ጆ ፒትስ አደጋውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን አውሎ ነፋሱ ያስከተለውን ጉዳት “እጅግ አደገኛ ክስተት” ሲሉ ገልጸውታል።

ችግሩን ለመከላከል ተጨማሪ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን በማሰማራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቴነስ የተከሰተው አውሎ ነፋስ በአሁኑ ወቅት ከ60 ሺሕ በላይ ሰዎች ከሃይል አቅርቦት ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉም በዘገባው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም