በፓሪስ ኦሊምፒክ ለሚሳተፉ አትሌቶች የአበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር ቀደም ብሎ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
በፓሪስ ኦሊምፒክ ለሚሳተፉ አትሌቶች የአበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር ቀደም ብሎ ይጀመራል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 30/2016 (ኢዜአ)፦ በፓሪስ ኦሊምፒክ ለሚሳተፉ አትሌቶች የአበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር ቀደም ብሎ የሚጀመር መሆኑን የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ከአበረታች ቅመም ጋር በተያያዘ ስምንት አትሌቶች ቅጣት የተላለፈባቸው ሲሆን ሁለት አትሌቶችም በጊዜያዊነት ታግደዋል።
እገዳ የተጣለባቸውን አትሌቶች በሚመለከትም ጉዳያቸው በመጣራት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ገልጿል።
በኢትዮጵያ ከአበረታች ቅመሞች ጋር በተያያዘዘ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በተመለከተ ኢዜአ የባለሥልጣኑን ዋና ዳይሬከተር መኮንን ይደርሳል አነጋግሯል።
የኢትዮጵያ አትሌቶች ከአበረታች ቅመሞች ጋር በተገናኘ ቀደም ሲል ስማቸው እንደማይነሳ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ አሁን ላይ ግን እየተቀጡና እየታገዱ ያሉ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ለፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት ስፖርተኞችን የማስተማርና የማሰልጠን ስራ እየተከናወነ ሲሆን በውድድሩ ለሚሳተፉ አትሌቶችና ለልዑካኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ለመስጠት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ለተወዳዳሪ አትሌቶች የአበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር ከወዲሁ የሚጀመር መሆኑንም አረጋግጠዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ ከሆነ ከጥር ጀምሮ የምርመራና የቁጥጥር ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ይከናወናሉ።
ኢትዮጵያ በ2024 በፈረንሳይ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ውድድር በአትሌቲክስና የውሃ ዋና የምትሳተፍ ሲሆን በብስክሌት፣ በቴኳንዶና በጁዶ የማለፊያ ውጤት የሚያስመዘግቡ አትሌቶችም በውድድሩ የሚሳተፉ ይሆናል።