ኢትዮጵያ የኮፕ 28 ጉባኤን ለባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ስራዋ በአግባቡ ተጠቅማበታለች - አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የኮፕ 28 ጉባኤን ለባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ስራዋ በአግባቡ ተጠቅማበታለች - አምባሳደሮች
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 30/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ 28ኛውን የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (ኮፕ 28) ወዳጅን ማበራከትን ጨምሮ ለባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ስራ በአግባቡ የተጠቀመችበት መሆኑን በተለየዩ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ገለጹ።
28ኛው የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 28) ከሕዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው ላይ ከአገራት፣ ከንግድ ተቋማት፣ አየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች የተወጣጡ ከ97 ሺህ በላይ ልዑካን በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን መከላከል፣ የዓለምን ሙቀት በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ የመገደብ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሰላባ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን አቅም መገንባትና መደገፍ፣ እ.አ.አ በ2050 የበካይ ጋዝ ልቀትን ዜሮ ማድረስ በሚቻልበትና በሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ በመምከር ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያም በጉባኤው ላይ በመሳተፍ የአረንጓዴ ልማት ስራዋን በኮፕ 28 ጉባኤ ላይ ባለው የኢትዮጵያ አውደ ርእይ /ፓቪሊዮን/ እያስተዋወቀች ነው።
በዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢፌዴሪ ቆንስል ጀነራል አምባሳደር አክሊሉ ከበደ ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ የረጅም ጊዜ ዝግጅት ማድረጓንና ስራውን የሚያስተባበር ብሔራዊ ኮሚቴና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ማቋቋሟን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መርቀው የከፈቱትን የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ አውደ ርዕይ (ፓቪሊዮን) የበርካታ አገራት፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ልዑካን መጎብኘታቸውንና ከኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ተሞክሮ የሚሆኑ ስራዎችን ለመመልከት እንደቻሉ መግለጻቸውን አመልክተዋል።
የጉባኤው አዘጋጅ አገር የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ መሐመድ አል ናህያን ፓቪሊዮን መጎብኘታቸውን አስታውሰዋል።
በፓቪሊዮኑ በርካታ የሁለትዮሽ የጎንዮሽ ውይይቶች መካሄዳቸውንና በዚህም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እያከናወነች ያለውን ስራ ለጉባኤው ልዑካን በሚገባ ለማስረዳት መቻሉን ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጉባኤው ጎን የኩባ ፕሬዝዳንት ሚጉዌል ዲያዝ-ካኔልና የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ዲ ክሮ ጨምሮ ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር መወያየታቸውን አስታውሰዋል።
በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ያሉ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮችም ከአቻዎቻቸው ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶች በስፋት ማከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
በምስራቅ አፍሪካ 300 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ግዙፉ የንፋስ ኃይል ማመንጫ በ600 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ መገንባት የሚያስችል ስምምነት በገንዘብ ሚኒስቴርና አሜአ ፓወር ከተሰኘ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ኩባንያ መካከል መፈረሙን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያና ጣልያን በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸውንም በማስታወስ።
ኢትዮጵያ የባለ ብዙሃ ወገን መድረክ በሆነው የኮፕ 28 ጉባኤ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና አረንጓዴ ልማት እያከናወነች ያለውን ስራ ለማሳየት በሚገባ መጠቀም መቻሏን ነው አምባሳደሩ ያስረዱት።
እንደ ኮፕ 28 ያሉ ዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያን እውነታና ስራዎች ለተቀረው ዓለም ለማሳወቅና በጎ ገጽታዋን ለማሳየትና አጋሮች ለማብዛት መልካም አጋጣሚዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ አማካኝነት በባለ ብዝሃን ወገን የትብብር መድረኮችን ተሰሚነቷን ከፍ ለማድረግ እያከናወንች ያለችውን ስራ እንደምትቀጥል አመልክተዋል።
የኮፕ 28 ጉባኤ እስከ ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ የገለጹት አምባሳደሩ በተቀሩት ቀናት የኢትዮጵያን ፓቪሊዮን ለጉባኤው ልዑካንና በአገሪቷ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የማስጎብኘትና የሁለትዮሽ የጎንዮሽ ውይይቶች እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ፤ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ዲፕሎማሲን እንደ አንድ የዲፕሎማሲ መሳሪያ እየተጠቀመችበት እንደምትገኝ ጠቅሰው ኮፕ 28 የዚሁ የትኩረት አቅጣጫ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮዋን ወደ ጎረቤት አገራት ማስፋቷን ጠቅሰው በደቡብ ሱዳንም ባለፉት ዓመታት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን በበጎ መልኩ እንደሚያየውና የአገሪቷ ዜጎች ለተተከሉት ችግኞች አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረጉ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በጁባ የሚገኘው የወጣቶች ማዕከል ለችግኞች ክብካቤ ስራ እንደ ዋና ማሳያ ሊጠቀስ እንደሚችልም ነው አምባሳደር ነቢል በማሳያነት የጠቀሱት።
ደቡብ ሱዳን በተለያዩ ግዛቶቿ ለሚያጋጥማት የጎርፍ አደጋዎች ለመከላከል እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ የአከባቢ ጥበቃ ስራዎች ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም አመልክተዋል።