የወንጀል መከላከልና የምርመራ ስራዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየተከናወኑ ነው- ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 30/2016 (ኢዜአ)፦ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ስራዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በላቀ ሙያዊ ብቃት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በመሰረታዊ የሪፎርም ስራዎች ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

በተቋማቱ በተደረገው የሪፎርም ስራም በአገርና ሕዝብ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን ቀድሞ መከላከልና ተፈጽመውም ሲገኙ በላቀ የምርመራ ብቃት ተጣርቶ ለህግ የማቅረብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

በዚህም የሀገርንና የህዝብን ደህንነት በአስተማማኝነት መልኩ መጠበቅ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ፤ የፖሊስ የመጀመሪያ ሥራ መረጃ መር የኅብረተሰብ አገልግሎት ላይ የተመሰረተ የወንጀል መከላከል ተግባር በመሆኑ በዚሁ መሰረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዜጎች እና በአገር ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን በመከላከልና የምርመራ ስራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በላቀ ሙያዊ ብቃት እየተከናወኑ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የዜጎችን ደኅንነት በአስተማማኝ መልኩ በመጠበቅ እየተደረገ ባለው ጥረትም የኅብረተሰቡ ተሳተፎ የላቀ ሚና እንዳለው ጠቅሰው ይሄው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል።

የፖሊስ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ስራዎች ብቃት ባለው የሰው ኃይል እና ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

የአገሪቱን ብሎም የቀጣናውን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥም ከኢንተርፖል እንዲሁም ጎረቤት አገራት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም