የአዲስ አበባ ከተማ የመረብ ኳስ  ውድድር በትንሿ ስቴድየም ተጀመረ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29/2016(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ የመረብ ኳስ ውድድር በትንሿ ስቴድየም በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።

በአዲስ አበባ ከተማ የመረብ ኳስ( ቮሊቦል) ፌዴሬሽን አማካኝነት በተዘጋጀው በዚህ ውድድር በወንዶች አምስት ክለቦች በሴቶች አራት ክለቦች የሚሳተፉበት ሲሆን እስከ ታህሳስ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

በውድድሩ ማስጀመሪያ በወንዶች መቻል ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር ተጫውተው አዲስ አበባ ፖሊስ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በሴቶች ፌደራል ማረሚያ ቤት አዲስ ከተማን 3 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ ተወዳጅ የሆነውን የመረብ ኳስ ስፖርት ለማስፋፋት ቢሮው በቀጣይም  ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ዛሬ የተጀመረው ውድድር አዲስ አበባን ወክለው በሀገር አቀፍ እና አህጉር አቀፍ መድረክ ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የመረብ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ በላይነህ ተካ በበኩላቸው የክለቦች የመረብ ኳስ ውድድር ለረዥም ጊዜ ሳይካሄድ ቆይቶ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

የውድድሩ ቀጣይነትም በከተማ ደረጃ የመረብ ኳስ ስፖርት እንዲያድግ እና ለፕሪሚየር ሊግ አቅም የሚሆኑ ልጆችን ለማግኘት ስፖርቱ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በመረብ ኳስ (ሲቲካፕ) ውድድሩ በሴቶች ጌታ ዘሩ፣ ፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን፣ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማና ብሔራዊ አልኮል ይወዳደራሉ።

በወንዶች ደግሞ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፣ አቃቂ ክፍለ ከተማ፣ ብሔራዊ አልኮል፣ መቻል እና አዲስ አበባ ፖሊስ በውድድሩ እንደሚካፈሉ የአዲስ አበባ ከተማ የመረብ ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም