የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያየ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 29 /2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፍሪካ እና በመካለኛው ምስራቅ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የበይነ መረብ ውይይት አደረገ ፡፡
የውይይት መድረኩ የዲያስፖራው ማህበረሰብ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ንቁ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲያደርግ ግንዛቤን መፍጠር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል ፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፈን አርአያ ባደረጉት የውይይቱ መክፈቻ ንግግር ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተመካክሮ መግባባት ለሀገራችን መጻኢ ተስፋ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል ፡፡
በውይይቱ ስለ ሀገራዊ ምክክሩ መሰረታዊ ፅንሰ-ሀሳቦች ፣ በኮሚሽኑ ስለተከናወኑ አንኳር ተግባራት እና ኮሚሽኑ ስለሚገዛባቸው የህግ ማዕቀፎች ማብራርያ ተሰጥቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ የዲያስፖራ አባላት ጋር በትብብር ስለሚሰራባቸው መንገዶች ላይ ሀሳብ እና አስተያየቶች በውይይቱ ቀርበዋል፡፡
በመጪዎቹ ጊዜያት ኮሚሽኑ መሰል ውይይቶችን በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በማድረግ ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን እንደሚሰበሰብ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማህበራዊ ድኅረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡