የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በሚያደርግልን ድጋፍ የተረጋጋ ህይወት እየመራን ነው - ስደተኞች

ጎንደር ፤ ህዳር 29 /2016 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ መንግስትና  ህዝብ በሚያደርግልን ድጋፍ የተረጋጋ   ኑሮ ለመምራት  ችለናል ሲሉ በዳባት አለም ዋጭ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ የጎረቤት አገር ስደተኞች ተናገሩ፡፡

ስደተኞቹ የዳባትና አካባቢው ማህበረሰብ ባለፉት አራት ወራት ላደረገላቸው ሰብአዊ ድጋፍ የእውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር ዛሬ በመጠለያው  አካሂደዋል፡፡

የስደተኞች ተወካይ  አቶ ሰለሞን ተስፋማርያም በስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤  የኢትዮጵያ መንግስትና  የዳባት  አካባቢው ህዝብ ባለፉት አራት ወራት አለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች  እርዳታ ባቋረጡበት ወቅት ያደረጉላቸው ድጋፍና እንክብካቤ በታሪክ ሲታወስ የሚኖር ነው። 

የምግብ እህልና ሌሎች ሰብአዊ ድጋፎችን በመጠለያው ለሚገኙ ስደተኞች በማቅረብ የመደጋገፍና የመተሳሰብ ጥልቅ ማህበራዊ እሴታቸውን በተግባር አሳይተውናል ሲሉ ገልጸዋል።

"ከአገሬ ኤርትራ ተሰድጄ ከመጣሁ ጀምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ ከአቀባበል ጀምሮ ያደረጉልን ድጋፍ ኢትዮጵያን እንደ ሀገሬ እንድመለከት አድርጎኛል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፊወሪ እቁባይ ናቸው፡፡

"ማህበረሰቡ ለስደተኞች የሚያደርገው እገዛና እንክብካቤ ፍጹም ያለስጋት የተረጋጋ ህይወት እንድንኖር አድርጎናል" ያሉት ወይዘሮ ፊወሪ፤ እርዳታ በተቋረጠበት ወቅት ለእኛንና ለልጆቻችን የተለየ ድጋፍ በማድረግ ተንከባክበውናል ብለዋል፡፡

ሌላዋ ስደተኛ ወይዘሮ ዮዲት አጽብኃ ፤  የአካባቢው ማህብረሰብ ለስደተኛው የሚያሳየው ፍቅርና  መተሳሰብ  ወንድማማችነትንና አብሮነትን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር ተወካይ አቶ አስማረ አበራ በእለቱ እንዳሉት ፤ ስደተኞቹ መብታቸው ተከብሮ ሰላማዊና የተረጋጋ ህይወት እንዲመሩ በማድረግ ረገድ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ስራ ተከናውኗል፡፡  

የዞኑ አስተዳደር በዳባት ከተማ 90 ሄክታር የሚሸፍን መሬት ለስደተኛ መጠለያ ቦታ በማዘጋጀት ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ መደገፉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በስደተኞቹና የአካባቢው ማህብረሰብ ያለውን ግንኙነት ከመደገፍ   የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙ  እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያው ከ20ሺህ በላይ የጎረቤት ሀገር ስደተኞች እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት የዳባት አለምዋጭ ስደተኛ መጠለያ አስተባባሪ አቶ ታምራት ደምሴ ናቸው፡፡ 

ለስደተኞቹ ይቀርብ የነበረው የምግብ እህል አቅርቦት ላለፉት አራት ወራት ተቋርጦ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ታምራት፤ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ ዳግም መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

የምግብ አህል አቅርቦቱ በተቋረጠበት ወቅት የአካባቢው ማህበረሰብ ስደተኞቹ ችግር እንዳይገጥማቸው በማሰብ ያልተቋረጠ የምግብ እህል ድጋፍ በማድረግ የጸና ፍቅሩን በተግባር ማረጋገጡን አንስተዋል፡፡

በምስጋና መርሃ ግብሩ ላይ የዞንና የወረዳ አመራር አባላት ፣ የአካባቢው ማህበረሰብና የስደተኞች ተወካዮች በተገኙበት በድጋፉ የነቃ ተሳትፈ ላበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች እውቅና ተሰጥቷል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም