የአክሱም ዩኒቨርሲቲ 1 ሺህ 692 አዲስ ተማሪዎችን ተቀበለ - ኢዜአ አማርኛ
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ 1 ሺህ 692 አዲስ ተማሪዎችን ተቀበለ

መቀሌ፤ ህዳር 29/2016(ኢዜአ)፡- የአክሱም ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡለትን 1 ሺህ 692 አዲስ ተማሪዎች መቀበሉን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙሉጌታ በሪሁ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ለ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የሚያስተምራቸውን ተማሪዎች የተቀበለው ባለፉት ሁለት ቀናት ነው።
ዩኒቨርሲቲው ከተቀበላቸው ተማሪዎች መካከል 635ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን ለማካሄድ የመኝታ፣የመማሪያና የመመገቢያ ክፍሎች ዝግጅት ማድረጉን አስረድተዋል።
እንዲሁም የቅጥር ግቢውን ጽዳትና የጥገና ሥራዎች አከናውኗል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን በተለያዩ ምክንያቶች አቋርጠው የነበሩ 4 ሺህ 122 ተማሪዎች ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑንም ዶክተር ሙሉጌታ ገልጸዋል።
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች አስተምሮ ማስመረቁን መረጃዎች ያመለክታሉ።
መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡለትን ከአንድ ሺህ በላይ የተፈጥሮና የማህበረሰብ ሳይንስ ተማሪዎችን መቀበል እንደጀመረ ትናንት መዘገባችን ይታወሳል።